አቤቱ ጉልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ። ጌታ ዓለቴ፥ አምባዬ፥ መድኃኒቴ፥ አምላኬ፥ በእርሱም የምተማመንበት ዓለቴ፥ ጋሻዬ፥ የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው። ምስጋና የሚገባውን ጌታን እጠራለሁ፥ ከጠላቶቼም እድናለሁ። የሞት ገመዶች ጠፍረው ያዙኝ፥ የጥፋት ጐርፍም አጥለቀለቀኝ፥ የሲኦል ገመዶች ተበተቡኝ፥ የሞት ወጥመዶችም ደረሱብኝ። በጨነቀኝ ጊዜ ጌታን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፥ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ። ምድርም ተንቀጠቀጠች ተናወጠችም፥ የተራሮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፥ ተናጉም እግዚአብሔርም ተቈጥቶአልና። ከአፍንጫው ጢስ ወጣ፥ ከአፉም የሚበላ እሳት ነደደ፥ ፍምም ከእርሱ በራ። ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ ወረደም፥ ጨለማ ከእግሩ በታች ነበረ። በኪሩቤልም ሠረገላ ላይ ተቀምጦ በረረ፥ በነፋስም ክንፍ አንዣበበ። መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ፥ በዙሪያውም ድንኳኑ፥ በውሃ የተሞሉ ጥቁር ደመናዎች ሸፍነውታል። በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ ደመናትና በረዶ የእሳት ፍምም አለፉ። ጌታ ከሰማያት አንጐደጐደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ። በረዶና የእሳት ፍምም፤ ፍላጻውን ላከ በተናቸውም፥ መብረቆችን አበዛ አወካቸውም።
መዝሙረ ዳዊት 18 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መዝሙረ ዳዊት 18:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos