እግዚአብሔር ሆይ! ኀይል የምትሰጠኝ አንተ ስለ ሆንክ፥ እወድሃለሁ። እግዚአብሔር አለቴ፥ አምባዬና አዳኜ ነው፤ አምላኬ የምጠጋበት አለቴ ነው፤ እርሱ ጋሻዬና የመዳኔ ቀን፥ ጠንካራ መመኪያም ነው። ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ እርሱም ከጠላቶቼ ያድነኛል። የሞት ጣር ከበበኝ፤ የጥፋት ጐርፍም አጥለቀለቀኝ። የሲኦል ገመድ ተበተበኝ፤ የሞት ወጥመድም ተጠመደብኝ። መከራ በደረሰብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ እንዲረዳኝም አምላኬን ለመንኩት፤ በመቅደሱ ሆኖ ድምፄን ሰማ፤ ጩኸቴንም አደመጠ። እግዚአብሔር ስለ ተቈጣ ምድር ተናወጠች፤ ተንቀጠቀጠችም፤ የተራሮች መሠረቶች ተናጉ፤ ተነቃነቁም። ከአፍንጫው የቊጣ ጢስ ወጣ፤ ከአፉም የሚባላ የእሳት ነበልባልና የሚያቃጥል ፍም ወጣ። ሰማይን ሰንጥቆ ወደ ታች ወረደ፤ ከእግሩም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረ። በኪሩቤል ላይ ሆኖ በረረ፤ በነፋስ ክንፎች ላይ ሆኖ ወደ ላይ መጠቀ። ሁለንተናውን በጨለማ ሸፈነ፤ በውሃ የተሞላ ጥቅጥቅ ያለ ደመና ከቦታል። በፊቱ ካለው ነጸብራቅ በረዶና የእሳት ብልጭታ ጥቅጥቅ ያለውን ደመና ሰንጥቆ ወጣ። እግዚአብሔር ከሰማይ አንጐደጐደ፤ ልዑል እግዚአብሔር ድምፁን አሰማ። ፍላጻውን ከቀስቱ አስፈነጠረ፤ ጠላቶቹንም በተናቸው፤ በመብረቁም ብልጭታ አሳደዳቸው። እግዚአብሔር ሆይ! ጠላቶችህን በገሠጽህ ጊዜ፥ የቊጣ ድምፅህንም ባሰማህ ጊዜ የውቅያኖስ ወለል ታየ፤ የምድርም መሠረት ተጋለጠ።
መጽሐፈ መዝሙር 18 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መዝሙር 18:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos