መዝሙረ ዳዊት 119:73-176

መዝሙረ ዳዊት 119:73-176 መቅካእኤ

እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ትእዛዛትህንም እማራለሁ። በቃልህ ታምኛለሁና የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይላቸዋል። አቤቱ፥ ፍርድህ ጽድቅ እንደ ሆነች፥ በእውነትህም እንዳስቸገርኸኝ አወቅሁ። ምሕረትህ ለመጽናናቴ ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባርያህ ይሁነው። ሕግህ ተድላዬ ናትና ቸርነትህ ትምጣልኝ፥ በሕይወትም ልኑር። ትዕቢተኞች በዓመፅ ጠምመውብኛልና ይፈሩ፥ እኔ ግን ትእዛዝህን አሰላስላለሁ። የሚፈሩህና ምስክሮችህን የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። እንዳላፍር ልቤ በሥርዓትህ የቀና ይሁን። ነፍሴ መድኃኒትህን ናፈቀች፥ በቃልህም ታመንሁ። መቼ ታጽናናኛለህ እያልሁ ዐይኖቼ ስለ ቃልህ ፈዘዙ። በጢስ ውስጥ እንዳለ አቁማዳ ሆኛለሁና፥ ሥርዓትህን ግን አልረሳሁም። የባርያህ ዘመኖች ስንት ናቸው? በሚያሳድዱኝስ ላይ መቼ ትፈርድልኛለህ? ኃጢአተኞች ጉድጓድ ቆፈሩልኝ፥ አቤቱ፥ እንደ ሕግህ ግን አይደለም። ትእዛዛትህ ሁሉ እውነት ናቸው፥ በዓመፅ አሳድደውኛል፥ እርዳኝ። ከምድር ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፥ እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም። እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ፥ የአፍህንም ምስክር እጠብቃለሁ። አቤቱ፥ ቃልህ በሰማይ ለዘለዓለም ይኖራል። እውነትህ ለልጅ ልጅ ናት፥ ምድርን መሠረትሃት እርሷም ትኖራለች። ሁሉም ባርያዎችህ ናቸውና ቀኑ በትእዛዝህ ይኖራል። ሕግህ ተድላዬ ባይሆን፥ ቀድሞ በጉስቁልናዬ በጠፋሁ ነበር። በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና ፍርድህን ለዘለዓለም አልረሳም። እኔ የአንተ ነኝ፥ ፍርድህን ፈልጌአለሁና አድነኝ። ኃጢአተኞች ያጠፉኝ ዘንድ ጠበቁኝ፥ ምስክርህን ግን መረመርሁ። የሥራን ሁሉ ፍጻሜ አየሁ፥ ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው። አቤቱ፥ ሕግህን እንደምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው። ለዘለዓለም ለእኔ ነውና ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ። ምስክርህ ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ። ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ ከክፉ መንገድ ሁሉ እግሬን ከለከልሁ። አስተምረኸኛልና ከፍርድህ አልራቅሁም። ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው፥ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ። ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፥ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ። ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው። የጽድቅህን ፍርድ እጠብቅ ዘንድ ማልሁ፥ አጸናሁም። እጅግ ተቸገርሁ፥ አቤቱ፥ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። አቤቱ፥ ከአፌ የሚወጣውን ቃል ውደድ፥ ፍርድህንም አስተምረኝ። ነፍሴ ሁልጊዜ በእጅህ ውስጥ ናት፥ ሕግህን ግን አልረሳሁም። ኃጢአተኞች ወጥመድን ዘረጉብኝ፥ ከትእዛዝህ ግን አልሳትሁም። የልቤ ደስታ ነውና ምስክርህን ለዘለዓለም ወረስሁ። ለዘለዓለም ለፍጻሜውም ትእዛዝህን አደርግ ዘንድ ልቤን አዘነበልሁ። ዓመፀኞችን ጠላሁ፥ ሕግን ግን ወደድሁ። አንተ ረዳቴና መጠጊያዬ ነህ፥ በቃልህም ተማመንሁ። እናንተ ኃጢአተኞች፥ ከእኔ ራቁ፥ የአምላኬንም ትእዛዝ ልፈልግ። እንደ ቃልህ ደግፈኝ፥ ሕያውም እሆናለሁ፥ ከተስፋዬም አልፈር። እርዳኝ እድናለሁም፥ ሁልጊዜም ሥርዓትህን እመረምራለሁ። ምኞታቸው ዓመፃ ነውና ከሥርዓትህ የሚርቁትን ሁሉ አጐሳቈልሃቸው። የምድርን ኃጢአተኞች ሁሉ እንደ ርኩሰት አጠፋሃቸው፥ ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ። ሥጋዬ አንተን ከመፍራት የተነሣ ደነገጠ፥ ከፍርድህ የተነሣ ፈርቻለሁ። ፍርድንና ጽድቅን ሠራሁ፥ ለሚያስጨንቁኝ አሳልፈህ አትስጠኝ። ባርያህን በመልካም ጠብቀው፥ ትዕቢተኞችም አይጋፉኝ። ዐይኖቼ ለማዳንህ፥ ለጽድቅህም ቃል ፈዘዙ። ለባርያህ እንደ ምሕረትህ አድርግ፥ ሥርዓትህንም አስተምረኝ። እኔ ባርያህ ነኝ፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ምስክርህንም አውቃለሁ። ለጌታ የሥራ ጊዜ ነው፥ ሕግህንም ሻሩት። ስለዚህ ከወርቅና ከዕንቁ ይልቅ ትእዛዝህን ወደድሁ። ስለዚህ ወደ ትእዛዝህ ሁሉ አቀናሁ፥ የዓመፅንም መንገድ ሁሉ ጠላሁ። ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው፥ ስለዚህ ነፍሴ ፈለገቻቸው። የቃልህ ፍቺ ያበራል፥ ሕፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል። አፌን ከፈትሁ፥ አለከለክሁም፥ ወደ ትእዛዝህ ናፍቄአለሁና። ስምህን ለሚወድዱ እንደምታደርገው ፍርድ፥ ወደ እኔ ተመልከት ማረኝም። አካሄዴን እንደ ቃልህ አቅና፥ ኃጢአትም ሁሉ አይግዛኝ። ከሰው ግፍ አድነኝ፥ ትእዛዝህንም እጠብቃለሁ። በባርያህ ላይ ፊትህን አብራ፥ ሥርዓትህንም አስተምረኝ። ሕግህን አልጠበቅሁምና የውኃ ፈሳሽ ከዐይኖቼ ፈሰሰ። አቤቱ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፥ ፍርድህም ቅን ነው። ምስክርህን በጽድቅ አዘዝህ፥ እጅግም ቅን ነው። ጠላቶቼ ቃልህን ረስተዋልና የቤትህ ቅንዓት አቀለጠኝ። ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው፥ ባርያህም ወደደው። እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፥ ትእዛዛትህን ግን አልረሳሁም። ጽድቅህ የዘለዓለም ጽድቅ ነው፥ ቃልህም እውነት ነው። መከራና ችግር አገኙኝ፥ ትእዛዛትህ ግን ተድላዬ ናቸው። ምስክርህ ለዘለዓለም ጽድቅ ነው፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ በሕይወትም አኑረኝ። በፍጹም ልቤ ጮኽሁ፥ አቤቱ፥ ስማኝ፥ ሥርዓትህን እፈልጋለሁ። ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አድነኝ፥ ምስክርህንም እጠብቃለሁ። ማለዳ ጮኽሁ፥ ቃልህንም ተስፋ አድርጌአለሁ። ቃልህን አስብ ዘንድ ዐይኖቼ ለመማለድ ቀደሙ። አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ ድምፄን ስማ፥ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ። በዓመፃ የሚያሳድዱኝ ቀረቡ፥ ከሕግህም ራቁ። አቤቱ፥ አንተ ቅርብ ነህ፥ መንገዶችህም ሁሉ ቅኖች ናቸው። ከዘለዓለም እንደ መሠረትኸው ከቀድሞ ጀምሮ ከምስክርህ የተነሣ አወቅሁ። ሕግህን አልረሳሁምና ችግሬን ተመልከት አድነኝም። ፍርዴን ፍረድ አድነኝም፥ ስለ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። መድኃኒት ከኀጥኣን ሩቅ ነው፥ ሥርዓትህን አልፈለጉምና። አቤቱ፥ ቸርነትህ እጅግ ብዙ ነው፥ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ። ያሳደዱኝና ያስጨነቁኝ ብዙዎች ናቸው፥ ከምስክር ግን ፈቀቅ አላልሁም። ቃልህን አልጠበቁምና ሰነፎችን አይቼ አዘንሁ። ትእዛዝህን እንደ ወደድሁ ተመልከት፥ አቤቱ፥ በምሕረትህ ሕያው አድርገኝ። የቃልህ መጀመሪያ እውነት ነው፥ የጽድቅህም ፍርድ ሁሉ ለዘለዓለም ነው። ገዢዎች በከንቱ አሳደዱኝ፥ ከቃልህ የተነሣ ግን ልቤ ደነገጠብኝ። ብዙ ምርኮ እንዳገኘ በቃልህ ደስ አለኝ። ዓመፃን ጠላሁ ተጸየፍሁም፥ ሕግህን ግን ወደድሁ። ስለ ጽድቅህ ፍርድ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ። ሕግህን ለሚወድዱ ብዙ ሰላም ነው፥ ዕንቅፋትም የለባቸውም። አቤቱ፥ ማዳንህን ተስፋ አደርግሁ፥ ትእዛዛትህንም ጠበቅሁ። ነፍሴ ምስክርህን ጠበቀች እጅግም ወደደችው። መንገዶቼ ሁሉ በፊትህ ናቸውና ትእዛዝህንና ምስክርህን ጠበቅሁ። አቤቱ፥ ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትቅረብ፥ እንደ ቃልህም አስተዋይ አድርገኝ። ልመናዬ ወደ ፊትህ ትድረስ፥ እንደ ቃልህ አድነኝ። ሥርዓትህን አስተምረኸኛልና ከንፈሮቼ ምስጋናን አወጡ። ትእዛዛትህ ሁሉ ጽድቅ ናቸውና አንደበቴ ቃልህን ተናገረ። ትእዛዛትህን መርጫለሁና እጅህ የሚያድነኝ ይሁን። አቤቱ፥ ማዳንህን ናፈቅሁ፥ ሕግህም ተድላዬ ነው። ነፍሴ ትኑርልኝ ታመሰግንህማለች፥ ፍርድህም ይርዳኝ። እንደ ጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ፥ ትእዛዛትህን አልረሳሁምና ባርያህን ፈልገው።