መዝሙረ ዳዊት 106:16-33

መዝሙረ ዳዊት 106:16-33 መቅካእኤ

ሙሴንም፥ ጌታ የቀደሰውንም አሮንን በሰፈር ተመቀኙአቸው። ምድርም ተከፈተች ዳታንንም ዋጠችው፥ የአቤሮንንም ወገን ደፈነች፥ በማኅበራቸውም እሳት ነደደች፥ ነበልባም ክፉዎችን አቃጠላቸው። በኮሬብም ጥጃን ሠሩ፥ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ። ሣርም በሚበላ በበሬ ምሳሌ ክብራቸውን ለወጡ። ታላቅ ነገርንም በግብጽ፥ ድንቅንም በካም ምድር፥ ግሩም ነገርንም በቀይ ባሕር ያደረገውን ያዳናቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ። እንዳያጠፋቸው ቁጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ፥ ያጠፋቸው እንደ ነበረ ተናገረ። የምትወደደውን ምድር ናቁ፥ በቃሉም አልታመኑም፥ በድንኳኖቻቸውም ውስጥ አንጐራጐሩ፥ የጌታን ቃል አልሰሙም። በምድረ በዳም ይጥላቸው ዘንድ፥ ዘራቸውንም በአሕዛብ መካከል ይጥል ዘንድ፥ በየአገሩም ይበትናቸው ዘንድ፥ እጁን አነሣባቸው። ከባዓል ፔዖርም ጋር ተጣበቁ፥ የሙታንንም መሥዋዕት በሉ፥ በሥራቸውም አስመረሩት፥ ቸነፈርም በላያቸው በዛ። ፊንሐስም ተነሥቶ ፈረደባቸው፥ ቸነፈሩም ተወ፥ ያም እስከ ዘለዓለም ለልጅ ልጅ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት። በክርክር ውኃ ዘንድም አስቈጡት፥ መንፈሱን አስመርረዋታልና፥ በእነርሱም የተነሣ ሙሴ ተበሳጨ፥ በከንፈሮቹም ያለማስተዋል ተናገረ።