መዝሙረ ዳዊት 104:18-35

መዝሙረ ዳዊት 104:18-35 መቅካእኤ

ረጃጅም ተራራዎች ለዋላዎች፥ ድንጋዮችም ለእሽኮኮች መሸሻ ናቸው። ወቅቶችን ለማመልከት ጨረቃን አደረግህ፥ ፀሐይም መግቢያውን ያውቃል። ጨለማን ታስቀምጣለህ፥ ሌሊትም ይሆናል፥ በእርሱም የዱር አራዊት ሁሉ ይወጡበታል። የአንበሳ ግልገሎች ለመንጠቅ ይጮኻሉ፥ ከእግዚአብሔርም ምግባቸውን ይሻሉ። ፀሐይ ስትወጣ ይሰበሰባሉ፥ በየዋሻቸውም ይተኛሉ። ሰው ወደ ተግባሩ፥ እስኪመሽም ድረስ ወደ ሥራው ይወጣል። አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፥ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፥ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች። ይህች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት፥ በዚያ ስፍር ቍጥር የሌለው ተንቀሳቃሽ፥ ታላላቆችና ታናናሾች እንስሶች አሉ። በዚያ ላይ መርከቦች ይሄዳሉ፥ በዚያም ላይ የፈጠርኸው ዘንዶ ያጫውትሃል። ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸው ዘንድ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ። በምትሰጣቸውም ጊዜ ይሰበስባሉ፥ እጅህን ትከፍታለህ፥ ከመልካም ነገርም ይጠግባሉ። ፊትህን ስትሰውር ይደነግጣሉ፥ ነፍሳቸውን ታወጣለህ ይሞታሉም፥ ወደ አፈራቸውም ይመለሳሉ። መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም፥ የምድርንም ፊት ታድሳለህ። የጌታ ክብር ለዘለዓለም ይሁን፥ ጌታ በሥራው ደስ ይለዋል። ምድርን ያያል እንድትንቀጠቀጥም ያደርጋል፥ ተራሮችን ይዳስሳል፥ ይጤሳሉም። በሕይወቴ ሳለሁ ለጌታ እቀኛለሁ፥ ለአምላኬም በምኖርበት ዘመን ሁሉ እዘምራለሁ። ቃሌ ለእርሱ ይጣፍጠው፥ እኔም በጌታ ደስ ይለኛል። ኀጥኣን ከምድር ይጥፉ፥ ዓመፀኞች ከእንግዲህ አይገኙ። ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ። ሃሌ ሉያ።