መጽሐፈ ምሳሌ 28
28
1ክፉ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፥
ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ተማምኖ ይኖራል።
2አገሪቱ ዓመፀኛ ስትሆን መሪዎችዋ ብዙ ሆኑ፥
በአስተዋይና በአዋቂ ሰው ግን ዘመንዋ ይረዝማል።
3ድሆችን የሚያስጨንቅ ድሃ#28፥3 በፊት ድሃ የነበረ ሰው። ሰው
እህልን እንደሚያጠፋ እንደ ዶፍ ዝናብ ነው።
4ሕግን የሚተዉ ሰዎች ክፉዎችን ያመሰግናሉ፥
ሕግ ጠባቂዎች ግን ይቃወሟቸዋል።
5ክፉዎች ሰዎች ፍትሕን አያስተውሉም፥
ጌታን የሚሹ ግን ሁሉን ያስተውላሉ።
6በጠማማ መንገድ ከሚሄድ ሀብታም
ያለ ነውር የሚሄድ ድሀ ይሻላል።
7ሕግን የሚጠብቅ አስተዋይ ልጅ ነው፥
ራሳቸውን የማይቆጣጠሩትን የሚከተል ግን አባቱን ያሳፍራል።
8ሀብቱን በአራጣ ብዛትና በቅሚያ የሚያበዛ
ለድሀ ለሚራራ ያከማችለታል።
9ሕግን ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ
ጸሎቱ እንኳን ሳይቀር አስጸያፊ ናት።
10ቅኖችን በክፉ መንገድ የሚያስት፥
እርሱ ወደ ጉድጓዱ ይወድቃል፥
ፍጹማን ግን መልካም ነገርን ይወርሳሉ።
11ሀብታም ሰው ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል፥
አስተዋይ ድሀ ግን ይመረምረዋል።
12ጻድቃን ድል ባደረጉ ጊዜ ብዙ ክብር አለ፥
ክፉዎች ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ ግን ሰው ይሸሸጋል።
13ጥፋቱን የሚሰውር አይለማም፥
የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል።
14ሁልጊዜ የሚጠነቀቅ ሰው ብፁዕ ነው፥
ልቡን የሚያጸና ግን በክፉ ላይ ይወድቃል።
15በድሀ ሕዝብ ላይ የሚገዛ ክፉ መሪ
እንደሚያገሣ አንበሳና እንደ ተራበ ድብ ነው።
16አእምሮ የጐደለው መኰንን ትልቅ ግፈኛ ነው፥
ግፍን የሚጠላ ግን ብዙ ዘመን ይኖራል።
17የሰው ደም ያለበት ሰው እስከጉድጓድ ይሸሻል፥
ማንም አያስጠጋውም።
18በቅንነት የሚሄድ ይድናል፥
በጠማምነት የሚሄድ ግን ወዲያው ይወድቃል።
19ምድሩን የሚያርስ እንጀራ ይጠግባል፥
የማይረቡ ሰዎችን የሚከተል ግን ድህነት ይሞላበታል።
20የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፥
ሀብታም ለመሆን የሚቸኩል ግን ሳይቀጣ አይቀርም።
21ማዳላት መልካም አይደለም፥ አንዳንድ ሰው ግን ለቁራሽ ሲል#28፥21 ለጉቦ ሲል። ጥፋት ይፈጽማል።
22ምቀኛ ሰው ሀብታም ለመሆን ይጣደፋል
ችጋርም እንደሚመጣበት አያውቅም።
23በምላሱ ከሚሸነግል ይልቅ
ሰውን የሚገሥጽ በኋላ ሞገስ ያገኛል።
24ከአባቱና ከእናቱ እየሰረቀ፦ “አላጠፋሁም” የሚል
የአጥፊ ሰው ባልንጀራ ነው።
25ስግብግብ ሰው ክርክርን ያነሣሣል፥
በጌታ የሚታመን ግን ይጠግባል።
26በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሞኝ ነው፥
በጥበብ የሚመላለስ ግን ይድናል።
27ለድሀ የሚሰጥ አያጣም፥
በድሆች ላይ ዐይኖቹን የሚጨፍን ግን እጅግ ይረገማል።
28ክፉዎች በተነሡ ጊዜ ሰዎች ይሸሸጋሉ፥
እነርሱ በጠፉ ጊዜ ግን ጻድቃን ይበዛሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 28: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ