መጽሐፈ ምሳሌ 27
27
1 #
ያዕ. 4፥13-16። ቀኑ ምን እንደሚያመጣ አታውቅምና
ነገ በሚሆነው አትመካ።
2ሌላ ያመስግንህ እንጂ ከአንተ አፍ አይውጣ፥
ባዕድ ሰው እንጂ ከንፈርህ አይሁን።
3ድንጋይ ከባድ ነው አሸዋም እንዲሁ፥
ከሁለቱ ግን የሞኝ ቁጣ ይከብዳል።
4ቁጣ ጭካኔን ያስከትላል፥ ንዴትም እንደ ጎርፍ ነው፥
በቅንዓት ፊት ግን ማን መቆም ይችላል?
5ግልጽ ተግሣጽ
ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል።
6የወዳጅ ማቁሰል ለክፉ አይሰጥም፥
የጠላት መሳም ግን የውሸት ነው።
7የጠገበች ነፍስ የማር ወላላ ትረግጣለች፥
ለተራበች ነፍስ ግን የመረረ ነገር እንኳ ጣፋጭ ነው።
8ከቦታው ርቆ የሚሄድ ሰው
ከጎጆዋ ርቃ እንደምትበርር ወፍ ነው።
9ሽቱና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፥
ነፍስም በወዳጅ ምክር ደስ ይላታል።
10ወዳጅህንና የአባትህን ወዳጅ አትተው፥
በመከራህም ቀን ወደ ወንድምህ ቤት አትግባ፥
የቀረበ ወዳጅ ከራቀ ወንድም ይሻላል።
11ልጄ ሆይ፥ ጠቢብ ሁን፥ ልቤንም ደስ አሰኘው፥
ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ።
12ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፥
አላዋቂዎች ግን አልፈው ይሄዱና ይጐዳሉ።
13ለማያውቀው ከተዋሰ ሰው ልብሱን ውሰድ፥
ለእንግዳ ሰው የተዋሰውንም ለመያዣነት አስቀረው።
14በማለዳ ባልንጀራውን በታላቅ ድምጽ የሚባርክ ሰው
እንደሚራገም ያህል ነው።
15በዝናብ ቀን የሚያንጠባጥብ ቤትና ጠበኛ ሴት አንድ ናቸው፥
16እርሷንም መከልከል
ነፍስን መከልከልና ዘይትን በቀኝ እጅ መጨበጥ ነው።
17ብረት ብረትን ይስለዋል፥
ሰውም ባልንጀራውን እንዲሁ።
18በለሱን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል፥
ጌታውንም የሚጠብቅ ይከብራል።
19ውኃ ፊትን እንደሚያሳይ፥
እንዲሁ የሰው ልብ ለሰው ይታያል።
20ሲኦልና ጥፋት እንደማይጠግቡ፥
እንዲሁ የሰው ዐይን አይጠግብም።
21ብር በእሳት ወርቅም በማቅለጫ ይፈተናል፥
ሰውም በሚያመሰገኑት ሰዎች አፍ ይፈተናል።
22ሰነፍን በሙቀጫ ውስጥ ከእህል ጋር በዘነዘና ብትወቅጠው፥
ሞኝነቱ ከእርሱ አይርቅም።
23የበጎችህን ሁኔታ አስተውለህ እወቅ፥
በከብቶችህም ላይ ልብህን አኑር፥
24ሃብት ለዘለዓለም አይኖርምና፥
ዘውድም ለትውልድ ሁሉ አይጸናምና።
25ደረቅ ሣር በታጨደ ጊዜ፥ አዲስ ለምለም በታየ ጊዜ፥
ከተራራውም ቡቃያ በተሰበሰበ ጊዜ
26በጎች ለልብስህ
ፍየሎችም የእርሻ ዋጋ ይሆናሉ።
27ለሲሳይህ ለቤተ ሰቦችህም ሲሳይ
ለሴት አገልጋዮችህ ምግብ የፍየል ወተት ይበቃል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 27: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ