መጽሐፈ ምሳሌ 22
22
1መልካም ስም ከብዙ ሃብት ይሻላል፥
መልካም ሞገስም ከብርና ከወርቅ ይበልጣል።
2ሀብታምና ድሀ ይገናኛሉ፥
ሁለቱንም የፈጠራቸው ጌታ ነው።
3ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፥
አላዋቂዎች ግን አልፈው ይሄዱና ይጐዳሉ።
4የትሕትናና ጌታን የመፍራት ውጤት
ሀብት፥ ክብርና ሕይወት ናቸው።
5እሾህና ወጥመድ በጠማማ ሰው መንገድ ላይ ይገኛሉ፥
ነፍሱን ግን የሚጠብቅ ከእነርሱ ይርቃል።
6 #
ሲራ. 6፥18። ልጅን ሊሄድ በሚገባው መንገድ ምራው፥
በሸመገለም ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።
7ሀብታም ድሆችን ይገዛል፥
ተበዳሪም የአበዳሪ ጥገኛ ነው።
8ክፋትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል፥
የቁጣውም በትር ይጠፋል።
9ርኅሩህ የተባረከ ይሆናል፥
ከእንጀራው ለድሀ ሰጥቶአልና።
10ፌዘኛን ብታስወጣ ክርክር ይቆማል፥
ጠብና ስድብም ያልቃል።
11የልብን ንጽሕናን የሚወድና ንግግሩ ለዛ ያለው ሰው፥
ንጉሥ ወዳጁ ይሆናል።
12የጌታ ዐይኖች እውቀትን ይጠብቃሉ፥
የአታላዩን ቃላት ግን ይገለብጣል።
13ሰነፍ ሰው፦ “ውጪ አንበሳ አለ፤
ብወጣ፥ በመንገዱ ላይ እሞታለሁ”#22፥13 ከስንፍናው ብዛት ወጥቶ ላለመሥራት ሰበብ ይፈጥራል። ይላል።
14የአመንዝራ ሴት አፍ የጠለቀ ጉድጓድ ነው፥
ጌታ የተቈጣው በውስጡ ይወድቃል።
15ቂልነት በልጅ ልብ ውስጥ ተተብትቧል፥
የተግሣጽ በትር ግን ነፃ ያደርገዋል።
16ለራሱ ጥቅም ሲል ድሀን የሚጐዳ፥
ለሀብታም የሚሰጥ፥ እርሱ ወደ ድህነት ይወድቃል።
17ጆሮህን አዘንብለህ የጠቢባንን ቃላት ስማ፥
ልብህንም ወደ እውቀቴ አድርግ፥
18እነርሱን በውስጥህ ብትጠብቅ፥
በከንፈሮችህም ላይ የተዘጋጁ ቢሆኑ፥ አስደሳች ነገር ይሆንልሃልና።
19እምነትህ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ
እነሆ እነርሱን ዛሬ አስታወቅሁህ።
20-21የእውነትን ቃል እርግጥነት አስታውቅህ ዘንድ፥
ለሚጠይቅህም እውነትን ቃል መመለስ ይቻልህ ዘንድ፥
በምክርና በእውቀት ሠላሳ ምሳሌዎችን አልጻፍሁልህምን?
22ድሀን አትግፈፈው ድሀ ነውና፥
ችግረኛውንም በበር አትጨቁነው፥
23ምክንያቱም ጌታ ለእነርሱ ይሟገታልና፥
የቀሙአቸውንም ሰዎች ሕይወት ይቀማልና።
24ከቁጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፥
ከንዴተኛም ጋር አትሂድ፥
25መንገዱን ተምረህ፥
ለነፍስህም ወጥመድ እንዳታገኝህ።
26የምር ቃል እንደሚገቡ፥
ለባለ ዕዳዎች እንደሚዋሱ አትሁን፥
27መክፈል ባትችል፥
ለምን የምትተኛበት አልጋ ይወሰድብሃል?
28አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፋልስ።
29በሥራው ብልህ ሰው ትመለከታለህን?
በነገሥታት ፊት ያገለግላል፥
በተራ ሰዎችም ፊት ሊያገለግል አይቆምም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 22: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ