የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 23

23
1ከባለ ሥልጣን ጋር ለመብላት በተቀመጥህ ጊዜ፥
በፊትህ ያለውን በደኅና አስተውል፥
2ሰውነትህም ቢጎመጅ፥
በጉሮሮህ ላይ ካራ አድርግ።#23፥2 ራስህን ተቆጣጠር።
3ጣፋጩ መብል አይመርህ
የሐሰት እንጀራ ነውና።
4ሀብታም ለመሆን አትድከም፥
የገዛ ራስህን ማስተዋል ተው።
5ቀና ብለህ እያየኸው ይጠፋል፥
ወደ ሰማይ እንደሚበርር ንስር
ለራሱ ክንፍ ያበጃልና።
6የንፉግን ሰው እንጀራ አትብላ፥
ጣፋጩ መብልም አይመርህ፥
7በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፥
ብላ ጠጣ ይልሃል፥ ልቡ ግን ካንተ ጋር አይደለም።
8የበላኸውን መብል ትተፋዋለህ፥
ያማረውንም ቃልህን ታጠፋዋለህ።
9በሞኝ ጆሮ ምንም አትናገር፥
በቃልህ ጥበብ ያፌዛልና።
10የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ፥
ወደ ድሀ አደጎች እርሻ አትግባ፥
11ታዳጊአቸው ኃያል ነውና፥
እርሱም ፍርዳቸውን ከአንተ ጋር ይፋረዳልና።
12ልብህን ለምክር ስጥ፥
ጆሮህንም እንዲሁ ለእውቀት ቃላት።
13ልጅን ከመቅጣት ቸል አትበል፥
በበትር ብትመታው አይሞትምና።
14በበትር ትመታዋለህ፥
ነፍሱንም ታድናለህ።
15ልጄ ሆይ፥ ልብህ ጠቢብ ቢሆን
የእኔም ልብ ደስ ይለዋል፥
16ከንፈሮችህም በቅን ቢናገሩ
ኩላሊቶቼ ደስ ይላቸዋል።
17ልብህ በኃጢአተኞች አይቅና፥
ነገር ግን ቀኑን ሙሉ ጌታን በመፍራት ኑር፥
18በእውነት መጨረሻህ ያምራልና፥
ተስፋህም አይጠፋምና።
19ልጄ ሆይ፥ ስማ፥ ጠቢብም ሁን፥
ልብህንም በቀናው መንገድ ምራ።
20ከወይን ጠጅ ጠጪዎች ጋር አትቀመጥ
እንዲሁም ሥጋ ከማይጠግቡ ጋር፥
21ሰካራሞችና ሆዳሞች ይደኸያሉና፥
የእንቅልፍም ብዛት የተቦጫጨቀ ጨርቅ ያስለብሳልና።
22የወለደህን አባትህን ስማ፥
እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት።
23እውነትን ገንዘብህ አድርግ፥ አትሽጣትም፥
ጥበብን ተግሣጽን ማስተዋልንም ግዛ።
24የጻድቅ አባት እጅግ ደስ ይለዋል፥
ጠቢብንም ልጅ የወለደ ሐሤትን ያገኛል።
25አባትህና እናትህ ደስ ይበላቸው፥
አንተንም የወለደች ደስ ይበላት።
26ልጄ ሆይ፥ ልብህን ስጠኝ፥
ዐይኖችህም መንገዴን ይውደዱ።
27ሴተኛ አዳሪ የጠለቀች ዐዘቅት ናትና፥
ዘማዊትም ሴት የጠበበች ጉድጓድ ናትና።
28እንደ ሌባ ታደባለች
የእምነተቢሶችንም ቍጥር ታበዛለች።
29ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው?
ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው?
ያለ ምክንያት መቁሰል ለማን ነው? የዐይን ቅላት ለማን ነው?
30የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን?
የተደባለቀ የወይንን ጠጅ ሳይታክቱ ለሚሞክሩ አይደለምን?
31ወደ ወይን ጠጅ አትመልከት
ሲቀላ፥ መልኩም በብርጭቆ ሲያንጸባርቅ፥
እየጣፈጠም ሲገባ።
32በኋላ እንደ እባብ ይነድፋል፥
እንደ እፉኝትም መርዙን ያሰራጫል።
33ዐይኖችህ ልዩ ነገሮችን ያያሉ፥
ልብህም ጠማማ ነገርን ይናገራል።
34በባሕር ውስጥ እንደ ተኛ ትሆናለህ፥
በመርከብም ምሶሶ ላይ እንደ ተኛ።
35መቱኝ፥ ያውም አልተሰማኝም፥
ደበደቡኝ፥ አላወቅሁምም።
መቼ እነሣለሁ?
ደግሞ ጨምሬ እፈልጋለሁ ትላለህ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ