መጽሐፈ ምሳሌ 20
20
1የወይን ጠጅ ፌዘኛ ያደርጋል፥ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል፥
በዚህም የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም።
2የንጉሥ ቁጣ እንደ አንበሳ ግሣት ነው፥
የሚያስቈጣውም ሰው የራሱን ነፍስ ይበድላል።
3ከክርክር ይርቅ ዘንድ ለሰው ክብሩ ነው፥
ሰነፍ ሁሉ ግን እንዲህ ባለ ነገር ይጣመራል።
4ታካች ሰው በብርድ ምክንያት አያርስም፥
ስለዚህ በመከር ይለምናል፥ ምንም አያገኝም።
5ምክር በሰው ልብ እንደ ጠሊቅ ውኃ ነው፥
አእምሮ ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል።
6ብዙ ሰዎች ቸርነታቸውን ያወራሉ፥
የታመነውን ሰው ግን ማን ያገኘዋል?
7ጻድቅ ያለ ነውር ይሄዳል፥
ልጆቹም ከእርሱ በኋላ ምስጉኖች ናቸው።
8በፍርድ ወንበር የተቀመጠ ንጉሥ
ክፉውን ሁሉ በዐይኖቹ ይበትናል።
9ልቤን አነጻሁ፥
ከኃጢአትም ጠራሁ የሚል ማን ነው?
10ሁለት ዓይነት ሚዛንና ሁለት ዓይነት መስፈሪያ፥
ሁለቱ በጌታ ፊት ርኩሳን ናቸው።
11ሕፃን ቅንና ንጹሕ መሆኑ
በሚያደርገው ሥራ ይታወቃል።
12የሚሰማ ጆሮንና የሚያይ ዓይንን፥
ሁለቱን ጌታ ፈጠራቸው።
13ድሀ እንዳትሆን እንቅልፍን አትውደድ፥
ዓይንህን ክፈት፥ እንጀራም ትጠግባለህ።
14ዕቃ የሚገዛ “አይረባም አይረባም” ብሎ ያራክሳል፥
ገዝቶ ሲመለስ ግን በገዛው ዕቃ ይኩራራል።
15ወርቅና ብዙ ቀይ ዕንቁ ይገኛል፥
የእውቀት ከንፈር ግን የከበረች ጌጥ ናት።
16ለማያውቀው ከተዋሰ ሰው ልብሱን ውሰድ፥
ለእንግዳ የተዋሰውንም እርሱን አግተው።
17የሐሰት እንጀራ ለሰው የጣፈጠ ነው፥
ከዚያ በኋላ ግን አፉ ጭንጫ ይሞላል።
18አሳብ በምክር ትጸናለች፥
በመልካምም ምክር ሰልፍ አድርግ።
19ዘዋሪ ሐሜተኛ ምሥጢርን ይገልጣል፥
ከንፈሩን የሚያሞጠሙጥ ሰውን አትገናኘው።
20አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ፥
በጽቅድቅ ጨለማ መብራቱ ይጠፋል።
21በመጀመሪያ ፈጥኖ የተከማቸ ርስት
ፍጻሜው አይባረክም።
22ክፉ እመልሳለሁ አትበል፥
ጌታን ተማመን፥ እርሱም ያድንሃል።
23ሁለት ዓይነት ሚዛን በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነው፥
ሐሰተኛ ሚዛንም መልካም አይደለም።
24የሰው አካሄዱ ከጌታ ዘንድ ነው፥
እንግዲስ ሰው መንገዱን እንዴት ያስተውላል?
25ሰው በችኰላ፦ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው ብሎ ቢሳል፥
ከተሳለም በኋላ ቢፀፀት ወጥመድ ነው።
26ጠቢብ ንጉሥ ኀጥኣንን በመንሽ ይበትናቸዋል፥
መንኰራኵሩንም በእነርሱ ላይ ያንኰራኩርባቸዋል።
27የሰው መንፈስ የጌታ መብራት ነው
የሆዱን ጉርጆች ሁሉ የሚመረምር።
28ቸርነትና እውነት ንጉሥን ይጠብቁታል፥
ዙፋኑም በቸርነት ይበረታል።
29የጎበዛዝት ክብር ጉልበታቸው ናት፥
የሽማግሌዎችም ጌጥ ሽበት ነው።
30የሰንበር ቁስል ክፉዎችን ያነጻል፥
ግርፋትም ወደ ሆድ ጉርጆች ይገባል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 20: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ