መጽሐፈ ምሳሌ 10
10
1የሰሎሞን ምሳሌዎች።
ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፥
አላዋቂ ልጅ ግን ለእናቱ ኀዘን ነው።
2በክፋት የተገኘ መዝገብ ጥቅም የለውም፥
ጽድቅ ግን ከሞት ያድናል።
3ጌታ የጻድቁን ነፍስ አያስርብም፥
የክፉዎችን ምኞት ግን ይገለብጣል።
4የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፥
የትጉ እጅ ግን ሀብታም ታደርጋለች።
5በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው፥
በመከር የሚተኛ ግን እርሱ ራሱን ያስነውራል።
6በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው፥
የክፉዎች አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል።
7የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው፥
የክፉ ስም ግን ይጠፋል።
8በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝን ይቀበላል፥
በከንፈሩ ሞኝ የሆነ ግን ይወድቃል።
9ያለ ነውር የሚመላለስ#10፥9 የሚኖር ተማምኖ ይሄዳል፥
መንገዱን የሚያጣምም ግን ይታወቃል።
10በዓይኑ የሚጠቅስ መከራን ያመጣል፥
ደፍሮ የሚገሥጽ ግን ሰላምን ያደርጋል#10፥10 ዕብራይስጡ ወደ ጥፋቱ ይሄዳል ይላል።።
11የጻድቅ አፍ የሕይወት ምንጭ ማፍለቂያ ናት፥
የክፉዎች አፍ ግን ዐመፅን ይሸፍናል።
12 #
ያዕ. 5፥20፤ 1ጴጥ. 4፥8። ጥላቻ ክርክርን ታስነሣለች፥
ፍቅር ግን በደልን ሁሉ ትከድናለች።
13በብልሃተኛ ከንፈር ጥበብ ትገኛለች፥
በትር ግን አእምሮ ለጐደለው ሰው ጀርባ ነው።
14ጠቢባን እውቀትን ያከማቻሉ፥
የአላዋቂ አፍ ግን ለጥፋት ይቀርባል።
15የሀብታም መዝገቡ የጸናች ከተማ ናት፥
የድሆች ውድቀት ድህነታቸው ነው።
16የጻድቅ ደመወዝ ለሕይወት ነው፥
የክፉ ገቢው ግን ለኃጢአት ነው።
17ተግሣጽን የሚጠብቅ በሕይወት መንገድ ይሄዳል፥
ዘለፋን የሚተው ግን ይስታል።
18ጥላቻን የሚከድን ሐሰተኛ ከንፈር አለው፥
ሐሜትንም የሚገልጥ አላዋቂ ነው።
19በቃል ብዛት ውስጥ መተላለፍ ሳይኖር አይቀርም፥
ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው።
20የጻድቅ ምላስ የተፈተነ ብር ነው፥
የክፉ ልብ ግን ዋጋ ቢስ ነው።
21የጻድቅ ከንፈሮች ብዙ ሰዎችን ይመግባሉ፥
አላዋቂዎች ግን ከማስተዋል ጉድለት የተነሣ ይሞታሉ።
22የጌታ በረከት ሀብታም ታደርጋለች፥
ኀዘንንም ከእርሷ ጋር አይጨምርም።
23ክፉ ነገር ማድረግ ለአላዋቂ ጨዋታ ነው፥
እንዲሁም ጥበብ ለአስተዋይ ነው።
24የክፉ ሰው ፍርሃት በላዩ ይመጣበታል፥
ለጻድቃንም ምኞታቸው ትሰጣቸዋለች።
25ዐውሎ ነፋስ ሲያልፍ ክፉ ሰው አይገኝም፥
ጻድቅ ግን የዘለዓለም መሠረት ነው።
26ሆምጣጤ ጥርስን፥ ጢስም ዓይንን እንደሚጐዳ፥
ሰነፍም ለላኩት እንዲሁ ነው።
27ጌታን መፍራት ዘመንን ታረዝማለች፥
የከፉዎች ዕድሜ ግን ታጥራለች።
28የጻድቃን አለኝታ ደስታ ነው፥
የክፉዎች ተስፋ ግን ይጠፋል።
29የጌታ መንገድ ያለ ነውር ለሚሄድ አምባ ነው፥
ክፋትን ለሚያደርጉ ግን ጥፋት ነው።
30ጻድቅ ለዘለዓለም አይናወጥም፥
ክፉዎች ግን በምድር ላይ አይቀመጡም።
31የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል፥
የመጥመም ምላስ ግን ትቈረጣለች።
32የጻድቅ ከንፈሮች ደስ የሚያሰኝ ነገርን ያውቃሉ፥
የክፉዎች አፍ ግን ጠማማ ነገር ይናገራል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 10: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ