ኦሪት ዘኍልቊ 8:15-26

ኦሪት ዘኍልቊ 8:15-26 መቅካእኤ

“ካነጻሓቸውና ለመወዝወዝም ቁርባን ካቀረብካቸው በኋላ ሌዋውያን የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ለመፈጸም ይገባሉ። እነርሱም ከእስራኤል ልጆች መካከል ፈጽሞ ለእኔ ተሰጥተዋልና፤ በእስራኤል ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ማኅፀን በሚከፍተው ሁሉ ፋንታ ለእኔ ወስጄአቸዋለሁ። በግብጽ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ በገደልሁበት ቀን የእስራኤልን ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ሰው ወይም እንስሳ፥ ለእኔ ቀድሼአቸዋለሁና የእኔ ናቸው። በእስራኤልም ልጆች በኵራት ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ወስጄአለሁ። የእስራኤልም ልጆች ወደ መቅደሱ በቀረቡ ጊዜ መቅሠፍት እንዳያገኛቸው፥ ለእስራኤል ልጆች እንዲያስተስርዩላቸው፥ የእስራኤልንም ልጆች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ እንዲሠሩ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለአሮንና ለልጆቹ ስጦታ አድርጌ ሰጥቼአቸዋለሁ።” ሙሴና አሮን የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲሁ በሌዋውያን ላይ አደረጉ፤ ጌታ ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉላቸው። ሌዋውያንም ከኃጢአት ራሳቸውን አነጹ፥ ልብሳቸውንም አጠቡ፤ አሮንም ለመወዝወዝ ቁርባን በጌታ ፊት አቀረባቸው፥ አሮንም እነርሱን ለማንጻት ማስተስረያ አደረገላቸው። ከዚያም በኋላ ሌዋውያን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በአሮንና በልጆቹ ፊት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ገቡ፤ ጌታ ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረጉላቸው። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “በሌዋውያን ላይ ይህ ተፈጻሚ ይሆንባቸዋል፤ ዕድሚያቸው ሀያ አምስት ዓመት የሆናቸውና ከዚያም በላይ ያሉት የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ለመፈጸም ይገባሉ። ዕድሜአቸውም ኀምሳ ዓመት ሲሞላ አገልግሎታቸውን ይተዋሉ፥ ከዚያም በኋላ አይሠሩም፤ ወንድሞቻቸው የተሰጣቸውን ግዴታ እንዲወጡ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይርዱአቸው እንጂ የድንኳኑን አገልግሎት አይሠሩ። በየአገልግሎታቸው በመደልደል በሌዋውያን ላይ እንዲሁ ታደርጋለህ።”