የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኍልቊ 13

13
ሰላዮች ወደ ከንዓን ምድር መላካቸው
1ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“ለእስራኤል ልጆች የምሰጣትን የከንዓንን ምድር እንዲሰልሉ ሰዎችን ላክ፤ ከአባቶች ነገድ ሁሉ እያንዳንዱ በመካከላቸው አለቃ የሆነ አንድ ሰው ትልካላችሁ።” 3ሙሴም እንደ ጌታ ትእዛዝ ከፋራን ምድረ በዳ ላካቸው፤ እነርሱም ሁሉ የእስራኤል ልጆች አለቆች ነበሩ። 4ስማቸውም ይህ ነበረ፤ ከሮቤል ነገድ የዘኩር ልጅ ሰሙኤል፤ 5ከስምዖን ነገድ የሱሬ ልጅ ሳፋጥ፤ 6ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፤ 7ከይሳኮር ነገድ የዮሴፍ ልጅ ይግዓል፤ 8ከኤፍሬም ነገድ የነዌ ልጅ ሆሴአ፤ 9ከብንያም ነገድ የራፉ ልጅ ፈልጢ፤ 10ከዛብሎን ነገድ የሰዲ ልጅ ጉዲኤል፤ 11ከዮሴፍ ነገድ እርሱም የምናሴ ነገድ የሱሲ ልጅ ጋዲ፤ 12ከዳን ነገድ የገማሊ ልጅ ዓሚኤል፤ 13ከአሴር ነገድ የሚካኤል ልጅ ሰቱር፤ 14ከንፍታሌም ነገድ የያቢ ልጅ ናቢ፤ 15ከጋድ ነገድ የማኪ ልጅ ጉዲኤል። 16ምድሪቱን እንዲሰልሉ ሙሴ የላካቸው ሰዎች ስሞቻቸው እነዚህ ነበሩ። ሙሴም የነዌን ልጅ ሆሴአን ኢያሱ ብሎ ጠራው።
17ሙሴም የከነዓንን ምድር እንዲሰልሉ ላካቸው፥ እነርሱንም እንዲህ አላቸው፦ “ከዚህ በኔጌብ በኩል አድርጋችሁ ውጡ፥ ወደ ተራራማውም አገር ሂዱ፤ 18ምድሪቱንም ምን እንደምትመስል፥ በእርሷም የሚኖሩ ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፥ ጥቂቶች ወይም ብዙዎች እንደ ሆኑ እዩ፤ 19እንዲሁም የሚኖሩባት ምድር መልካም ወይም ክፉ፥ የሚኖሩባቸውም ከተሞች ሰፈሮች ወይም የተመሸጉ አምባዎች እንደ ሆኑ፥ 20ምድሪቱም ለም ወይም መካን፥ ዛፍ ያለባት ወይም የሌለባት እንደ ሆነች ተመልከቱ፤ ከምድሪቱ ፍሬ አምጡ፤ አይዞአችሁ።” በዚያን ጊዜም ወይኑ አስቀድሞ ፍሬ የሚያፈራበት ወቅት ነበረ።
21ወጡም ምድሪቱንም ከጺን ምድረ በዳ ለሌብ ሐማት ቅርብ እስከሆነችው እስከ ረዓብ ድረስ ሰለሉ። 22በደቡብም በኩል ወጡ፥ ወደ ኬብሮንም ደረሱ፤ በዚያም የዔናቅ ልጆች አኪመን፥ ሴሲ፥ ተላሚ ነበሩ። ኬብሮንም በግብጽ ካለችው ከጣኔዎእ ከሰባት ዓመት በፊት የተቈረቈረች ከተማ ነበረች። 23ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጡ፥ ከዚያም ከወይኑ አንድ ሙሉ ዘለላ የነበረበትን አረግ ቈረጡ፥ ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በመሎጊያ ተሸከሙት፤ ደግሞም ከሮማኑ ከበለሱም አመጡ። 24የእስራኤል ልጆች ከዚያ ስለ ቈረጡት ዘለላ የዚያን ስፍራ ስም የኤሽኮል ሸለቆ ብለው ጠሩት።
ሰላዮቹ ያመጡት ወሬ
25ምድሪቱንም ሰልለው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ። 26ተጉዘውም በፋራን ምድረ በዳ በቃዴስ ወዳሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ መጡ፤ ወሬውንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ነገሩአቸው፥ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው። 27እንዲህም ብለው ነገሩት፦ “ወደ ላክኸን ምድር ገባን፥ እርሷም ወተትና ማር ታፈስሳለች፥ ፍሬዋም ይህ ነው። 28ነገር ግን በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ኃያላን ናቸው፤ ከተሞቻቸውም የተመሸጉ እጅግም ሰፋፊዎች ናቸው፤ ደግሞም በዚያ የዔናቅን ልጆች አየን። 29በደቡብም ምድር አማሌቅ ተቀምጦአል፤ በተራሮቹም ኬጢያዊና ኢያቡሳዊ አሞራዊም ተቀምጠዋል፤ ከነዓናዊም በባሕር ዳርና በዮርዳኖስ አጠገብ ተቀምጦአል።”
30ካሌብም ሕዝቡን በሙሴ ፊት ዝም አሰኘና፦ “ማሸነፍ እንችላለንና እንውጣ፥ እንውረሰው” አለ። 31ከእርሱ ጋር ወጥተው የነበሩት ሰዎች ግን፦ “ከእኛ ይልቅ እነርሱ ብርቱ ናቸውና በዚህ ሕዝብ ላይ መውጣት አንችልም” አሉ። 32ስለ ሰለሉአትም ምድር ክፉ ወሬ ለእስራኤል ልጆች አወሩ እንዲህም አሉ፦ “እኛ ዞረን የሰለልናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ምድር ናት፤ በእርሷም ዘንድ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ረጃጅም ሰዎች ናቸው። 33#ዘፍ. 6፥4።በዚያም ከኔፊሊም ወገን የሆኑትን ኔፊሊም፥ የዔናቅን ልጆች፥ አየን፤ እኛም በዓይናችን ግምት እንደ አንበጣዎች ነበርን፥ ደግሞም እኛ በዓይናቸው ዘንድ እንዲሁ ነበርን።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ