ባለማመናቸውም ተደነቀ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ ሁለት ሁለቱን ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው። ይህንንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “ለመንገዳችሁ ከበትር በስተቀር፥ እንጀራ ወይም ከረጢት ወይም ደግሞ ገንዘብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤ ጫማ አድርጉ፤ ነገር ግን ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ፤ ወደ አንድ ቤት በምትገቡበት ጊዜ ከዚያች ከተማ እስክትወጡ ድረስ እዚያው ቆዩ፤ የትኛውም ቦታ የማይቀበላችሁና የማይሰማችሁ ከሆነ፥ ከዚያ ስፍራ ስትወጡ ከእግራችሁ ሥር ያለውን ትቢያ በዚያ አራግፉ፤ ይህም ምስክር ይሆንባቸዋል።” እነርሱም ከዚያ ወጥተው፤ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ ሰበኩ፤ ብዙ አጋንንት አስወጡ፤ ብዙ ሕመምተኞችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ። የኢየሱስ ስም እየታወቀ በመምጣቱ፥ ንጉሥ ሄሮድስ ይህንኑ ሰማ። አንዳንዶችም፥ “የዚህ ዓይነት ታምር በእርሱ የሚሠራው መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ቢነሣ ነው” ይሉ ነበር። ሌሎቹም፥ “ኤልያስ ነው” አሉ። አንዳንዶች ደግሞ፥ “ከቀደምት ነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው” ይሉ ነበር። ሄሮድስ ነገሩን ሲሰማ ግን፥ እኔ ራሱን ያስቆረጥሁት ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቷአል አለ። ሄሮድስ ራሱ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱ ምክንያት፥ ተይዞ እንዲታሰር ትእዛዝ በመስጠት ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገብቶት ነበር። ዮሐንስ ሄሮድስን፥ “የወንድምህን ሚስት ታገባት ዘንድ ሕግ ይከለክልሃል” ይለው ነበርና። ሄሮድያዳም በዚህ ቂም ይዛበት ልታስገድለው ፈለገች፤ ነገር ግን አልሆነላትም። ምክንያቱም ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው መሆኑን ሄሮድስ በማወቁ ይፈራውና ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ሄሮድስ ቢታወክም በደስታ ያዳምጠው ነበር። በመጨረሻም አመቺ ቀን መጣ። ሄሮድስ በተወለደበት ዕለት ለከፍተኛ ሹማምንቱ፥ ለጦር አዛዦቹና በገሊላ ለታወቁ ታላላቅ ሰዎች ግብዣ አደረገ። የሄሮድያዳም ልጅ ገብታ በዘፈነች ጊዜ ሄሮድስንና ተጋባዦቹን ደስ አሰኘቻቸው፤ ንጉሡም ብላቴናዪቱን፥ “የምትፈልጊውን ሁሉ ጠይቂኝ እሰጥሻለሁ” አላት። ደግሞም “እስከ መንግሥቴ እኩሌታ ድረስ እንኳ ቢሆን፥ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ” ሲል በመሓላ ቃል ገባላት። እርሷም ወጥታ እናቷን፥ “ምን ልለምነው?” አለቻት። እናቷም፥ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ” አለቻት። ብላቴናዪቱም ወዲያው ፈጥና ወደ ንጉሡ በመመለስ፥ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አሁን በሳሕን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” አለችው። ንጉሡ በነገሩ እጅግ አዘነ፤ በተጋበዙት እንግዶች ፊት የመሐላ ቃሉን ለማጠፍ አልፈለገም። ስለዚህ አንዱን ወታደር በፍጥነት ልኮ፥ የዮሐንስን ራስ ቆርጦ እንዲያመጣ አዘዘው፤ እርሱም ሄዶ በወህኒ ቤቱ ውስጥ ራሱን ቆረጠ፤ በሳሕን አምጥቶ ለብላቴናዪቱ ሰጣት፤ ብላቴናዪቱም ለእናቷ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህን እንደ ሰሙ መጡ፤ ሬሳውንም ወስደው ቀበሩት።
የማርቆስ ወንጌል 6 ያንብቡ
ያዳምጡ የማርቆስ ወንጌል 6
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 6:6-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos