የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 6:6-29

ማርቆስ 6:6-29 NASV

ባለማመናቸውም ተደነቀ። ከዚያም ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። ዐሥራ ሁለቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ ሁለት ሁለቱን ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው። ይህንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “ለመንገዳችሁ ከበትር በቀር፣ እንጀራ ወይም ከረጢት ወይም ደግሞ ገንዘብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤ ጫማ አድርጉ፤ ነገር ግን ትርፍ እጀ ጠባብ አትልበሱ፤ ወደ አንድ ቤት በምትገቡበት ጊዜ ከዚያች ከተማ እስክትወጡ ድረስ እዚያው ቈዩ፤ የትኛውም ቦታ የማይቀበላችሁ ወይም የማይሰማችሁ ከሆነ፣ ከዚያ ስፍራ ስትወጡ ምስክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ በዚያ አራግፋችሁ ውጡ።” እነርሱም ከዚያ ወጥተው፤ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ ሰበኩ፤ ብዙ አጋንንት አስወጡ፤ ብዙ ሕመምተኞችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ። የኢየሱስ ስም እየታወቀ በመምጣቱ፣ ንጉሥ ሄሮድስ ይህንኑ ሰማ። አንዳንዶችም፣ “የዚህ ዐይነት ታምር በርሱ የሚሠራው መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ቢነሣ ነው” ይሉ ነበር። ሌሎቹም፣ “ኤልያስ ነው” አሉ። አንዳንዶች ደግሞ፣ “ከቀደምት ነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው” ይሉ ነበር። ሄሮድስ ነገሩን ሲሰማ ግን፣ “እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቷል!” አለ። ሄሮድስ ራሱ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱ ምክንያት፣ ተይዞ እንዲታሰር ትእዛዝ በመስጠት ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገብቶት ነበር። ዮሐንስ ሄሮድስን፣ “የወንድምህን ሚስት ታገባት ዘንድ ሕግ ይከለክልሃል” ይለው ነበርና። ሄሮድያዳም በዚህ ቂም ይዛበት ልታስገድለው ፈለገች፤ ነገር ግን አልሆነላትም። ምክንያቱም ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው መሆኑን ሄሮድስ በማወቁ ይፈራውና ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ሄሮድስ ቢታወክም በደስታ ያደምጠው ነበር። በመጨረሻም አመቺ ቀን መጣ። ሄሮድስ በተወለደበት ዕለት ለከፍተኛ ሹማምቱ፣ ለጦር አዛዦቹና በገሊላ ለታወቁ ታላላቅ ሰዎች ግብዣ አደረገ። የሄሮድያዳም ልጅ ገብታ በዘፈነች ጊዜ ሄሮድስንና ተጋባዦቹን ደስ አሠኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናዪቱን፣ “የምትፈልጊውን ሁሉ ጠይቂኝ እሰጥሻለሁ” አላት። ደግሞም “እስከ መንግሥቴ እኩሌታ ድረስ እንኳ ቢሆን፣ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ” ሲል በመሐላ ቃል ገባላት። እርሷም ወጥታ እናቷን፣ “ምን ልለምነው?” አለቻት። እናቷም፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ” አለቻት። ብላቴናዪቱም ወዲያው ፈጥና ወደ ንጉሡ በመመለስ፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አሁን በሳሕን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” አለችው። ንጉሡ በነገሩ እጅግ ዐዘነ፤ ይሁን እንጂ ስለ መሐላውና ከርሱ ጋራ ስለ ነበሩ እንግዶች ሲል ቃሉን ለማጠፍ አልፈለገም። ወዲያውኑም ንጉሡ አንዱን ወታደር በፍጥነት ልኮ፣ የዮሐንስን ራስ ቈርጦ እንዲያመጣ አዘዘው፤ እርሱም ሄዶ በወህኒ ቤቱ ውስጥ ራሱን ቈረጠ፤ በሳሕን አምጥቶ ለብላቴናዪቱ ሰጣት፤ ብላቴናዪቱም ለእናቷ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህን እንደ ሰሙ መጡ፤ ሬሳውንም ወስደው ቀበሩት።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች