የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማርቆስ ወንጌል 6:6-29

የማርቆስ ወንጌል 6:6-29 አማ05

ሕዝቡ ሳያምኑ በመቅረታቸው እጅግ ተገረመ፤ ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፤ ለመንገዳቸው ከበትር በቀር እንጀራም ሆነ ከረጢት፥ ገንዘብም በመቀነታቸው እንዳይዙ አዘዛቸው። እንዲህም አላቸው፤ “በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀጠባብ እንኳ አትልበሱ፤ በማናቸውም ስፍራ ወደ አንድ ሰው ቤት ስትገቡ፥ ያንን ስፍራ እስክትለቁ ድረስ በዚያው ቈዩ፤ ሰዎች በማይቀበሉአችሁና በማይሰሙአችሁ ቦታ ሁሉ የእግራችሁን አቧራ አራግፉና ከዚያ ወጥታችሁ ሂዱ፤ ይህም ለእነርሱ የማስጠንቀቂያ ምስክር ይሆንባቸዋል።” የተላኩትም ከዚያ ወጥተው፥ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ አስተማሩ። ብዙ አጋንንትንም አስወጡ፤ ብዙ ሰዎችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ። የኢየሱስ ዝና በሁሉም ዘንድ ስለ ታወቀ፥ ንጉሡ ሄሮድስ ስለ እርሱ ሰማ። አንዳንድ ሰዎች፥ “መጥምቁ ዮሐንስ ከሞት ተነሥቶአል፤ ስለዚህ ይህ ሁሉ ተአምራት በእርሱ ይደረጋል” ይሉ ነበር። ሌሎችም “ኤልያስ ነው፤” ይሉ ነበር፤ የቀሩትም ደግሞ “ከቀድሞዎቹ ነቢያት እንደ አንዱ ነው፤” ይሉ ነበር። ሄሮድስ ግን ይህን ሁሉ ሰምቶ፦ “ይህ እኔ አንገቱን ያስቈረጥኩት ዮሐንስ ነው፤ እነሆ! እርሱ ከሞት ተነሥቶአል፤” አለ። ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮዲያዳን ስለአገባ ዮሐንስን በእርስዋ ምክንያት አስይዞ በወህኒ ቤት አስሮት ነበር። ዮሐንስም የታሰረው፥ ሄሮድስን “የወንድምህን ሚስት ማግባትህ ተገቢ አይደለም!” ብሎት ስለ ነበር ነው። ሄሮዲያዳ በዚህ ተቀይማ ዮሐንስን ልታስገድለው ትፈልግ ነበር፤ ነገር ግን አልቻለችም። ሄሮድስ በመጀመሪያ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ መሆኑን ስለሚያውቅ ይፈራውና ይጠብቀውም ነበር። ሄሮድስ የዮሐንስን ንግግር በሰማ ቊጥር ይታወክ ነበር፤ ይሁን እንጂ በደስታ ይሰማው ነበር። ሄሮድስ የተወለደበትን ቀን ለማክበር ለመንግሥት ባለሥልጣኖች፥ ለጦር ሹማምንትና ለአንዳንድ የታወቁ የገሊላ ነዋሪዎች ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ ይህም ለሄሮዲያዳ ጥሩ አጋጣሚ ሆነላት፤ ስለዚህም የሄሮዲያዳ ልጅ ወደ ግብዣው አዳራሽ ገብታ እየጨፈረች ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ተጋባዦች አስደሰተች፤ ንጉሡም ልጅትዋን፦ “የምትፈልጊውን ማንኛውንም ነገር ጠይቂኝ፤ እሰጥሻለሁ” አላት፤ “የመንግሥቴንም እኩሌታ እንኳ ቢሆን፥ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ!” ሲል ማለላት። እርስዋም ወደ እናትዋ ሄዳ፥ “ምን ልጠይቅ?” አለቻት፤ እናትዋም “ ‘የመጥምቁ ዮሐንስ ራስ ይሰጠኝ፤’ ብለሽ ጠይቂ፤” አለቻት። ልጅትዋም ወዲያውኑ በፍጥነት ወደ ንጉሡ ተመልሳ፥ “የመጥምቁ ዮሐንስ ራስ በሳሕን ሆኖ አሁን እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ፤” ስትል ጠየቀች። ንጉሡ በዚህ ነገር በጣም አዘነ፤ ይሁን እንጂ በተጋባዦች ፊት ስላደረገው መሐላ የጠየቀችውን ሊከለክላት አልፈለገም። ስለዚህ ንጉሡ ወዲያውኑ አንዱን የዘብ ጠባቂ ወታደር የዮሐንስን ራስ ቈርጦ እንዲያመጣ ላከው፤ ወታደሩም ወደ ወህኒው ቤት ሄዶ የዮሐንስን ራስ ቈረጠ፤ የተቈረጠውንም ራስ በሳሕን አድርጎ አመጣና ለልጅትዋ ሰጣት፤ ልጅትዋም ለእናትዋ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ይህን በሰሙ ጊዜ መጡና በድኑን ወስደው ቀበሩት።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች