የማርቆስ ወንጌል 1:35-45

የማርቆስ ወንጌል 1:35-45 መቅካእኤ

ማለዳም ገና ጎሕ ሳይቀድ፥ ኢየሱስ ተነሥቶ ከቤት ወጣ፤ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራም ሄዶ ይጸልይ ጀመር። ስምዖንና ባልደረቦቹም ተከትለው ይፈልጉት ጀመር፤ ባገኙትም ጊዜ፥ “ሰዉ ሁሉ ይፈልግሃል” አሉት። እርሱም፥ “ከዚህ ተነሥተን በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች እንሂድ፤ እዚያም ልስበክ፤ የመጣሁት ለዚሁ ነውና” አላቸው። ስለዚህ ወደ ምኵራባቸው እየገባ በመስበክና አጋንንትን በማስወጣት በመላዋ ገሊላ ይዘዋወር ጀመር። አንድ ለምጻምም ወደ እርሱ ቀርቦ ከፊቱ በመንበርከክ፥ “ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ለመነው። ኢየሱስም ለሰውየው በመራራት እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፥ “እፈቅዳለሁ፥ ንጻ” አለው። እርሱም ወዲያው ከለምጹ ነጻ፤ ከበሽታውም ተፈወሰ። ኢየሱስም ሰውየውን አጥብቆ በማስጠንቀቅ እንዲህ ሲል አሰናበተው፤ “ለማንም አንድ ነገር እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ምስክር እንዲሆናቸው ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ስለ መንጻትህም ሙሴ ያዘዘውን መሥዋዕት አቅርብ” አለው። ሰውየው ግን በሄደበት ሁሉ ነገሩን በሰፊው አወራ፤ ወሬውንም አሠራጨ፤ በዚህ ምክንያት ኢየሱስ ወደ ማንኛውም ከተማ በግልጽ መግባት አልተቻለውም፤ ከዚህም የተነሣ ከከተማ ውጭ በሚገኙ ሰዋራ ቦታዎች መኖር ጀመረ፤ ሰዎች ግን ከየአቅጣጫው እርሱ ወዳለበት ይመጡ ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች