ትንቢተ ሚክያስ 3
3
ክፉ ገዢዎችና ነብያት
1እንዲህም አልሁ፦ የያዕቆብ አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዢዎች ሆይ፥ እባካችሁ ስሙኝ! ፍትሕን ማወቅ አይገባችሁምን?
2መልካሙን የምትጠሉ፥ ክፉውን የምትወዱ፤ ቁርበታቸውን ከላያቸው ላይ ገፈፋችሁ፥ ሥጋቸውንም ከአጥንታቸው ለያያችሁ፤
3የሕዝቤን ሥጋ በሉ፥ ቁርበታቸውን ከላያቸው ላይ ገፈፉ፥ አጥንታቸውን ሰበሩ፤ በአፍላል እንዳለ በድስትም ውስጥ እንደሚከተት ሥጋ ቆራርጠዋል።
4የዚያን ጊዜ ወደ ጌታ ይጮኻሉ፥ እርሱ ግን አይመልስላቸውም፤ በዚያን ጊዜ ፊቱን ከእነርሱ ይሰውራል፥ ሥራቸው ክፉ ነውና።
5ጌታ ሕዝቤን ስለሚያስቱ ነቢያት እንዲህ ይላል፦ ሰው ሲያበላቸው “ሰላም አለ” ይላሉ፤ ካላበላቸው ግን ጦርነት ሊያውጁበት ይነሣሉ።
6ስለዚህ ለእናንተ ራእይ የሌለው ሌሊት ይሆንባችኋል፥ የማትጠነቁሉበት ጨለማ ይሆንባችኋል፤ ፀሐይ በነቢያት ላይ ትጠልቅባቸዋለች፥ ቀኑም ይጨልምባቸዋል።
7ትንቢተኞች ይዋረዳሉ፥ ጠንቋዮችም ያፍራሉ፤ ሁሉም ከንፈራቸውን ይሸፍናሉ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ መልስ የለምና።
8እኔ ግን በደሉን ለያዕቆብ፥ ኃጢአቱንም ለእስራኤል እንድነግር በጌታ መንፈስ ኃይልን፥ ፍትህና ብርታት ተሞልቻለሁ።
9ፍትሕን የምትጠሉ፥ ትክክለኛውንም ነገር ሁሉ የምታጣምሙ እናንተ የያዕቆብ ቤት አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዢዎች ሆይ፥ እባካችሁ ይህን ስሙ፦
10ጽዮንን በደም፥ ኢየሩሳሌምንም በኃጢአት ይሠራሉ።
11አለቆችዋ በጉቦ ይፈርዳሉ፥ ካህናቷ በክፍያ ያስተምራሉ፥ ነቢዮችዋ በብር ያሟርታሉ፤ “ጌታ በመካከላችን አይደለምን? ክፉ ነገር በእኛ ላይ አይመጣብንም” እያሉ በጌታ ይደገፋሉ።
12 #
ኤር. 26፥18። ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፥ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፥ የቤቱም ተራራ የዱር ከፍታ ይሆናል።
Currently Selected:
ትንቢተ ሚክያስ 3: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ