ትንቢተ ሚክያስ 4
4
በመታዘዝ የሚመጣ ሰላምና መረጋጋት
1እንዲህም ይሆናል፥ በመጨረሻው ዘመን የጌታ ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶች በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ።
2ብዙዎች አሕዛብ መጥተው፦ ኑ ወደ ጌታ ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ እኛም በፍለጋው እንሄዳለን ይላሉ፤ ከጽዮን ሕግ፥ ከኢየሩሳሌምም የጌታ ቃል ይወጣልና።
3 #
ኢሳ. 2፥4፤ ኢዩ. 3፥10። በብዙዎች ሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፥ በሩቅም ባሉ በብርቱዎች መንግሥታት ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውን ወደ ማረሻ፥ ጦራቸውን ወደ ማጭድ ለመለወጥ ይቀጠቅጣሉ፤ መንግሥት በመንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፥ ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም።
4 #
ዘካ. 3፥10። እያንዳንዱ ሰው ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፥ የሚያስፈራውም የለም፤ የሠራዊት ጌታ አፍ ተናግሮአልና።
5ሕዝብ ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳልና፥ እኛ ግን በጌታ አምላካችን ስም ለዘለዓለም ዓለም እንሄዳለን።
ከስደት መልስ ለመታደስ የተገባላቸው ቃል
6በዚያ ቀን ይላል ጌታ፥ አንካሳይቱን እሰበስባለሁ፥ የተጣለችውንና የጎዳኋትን አከማቻለሁ፤
7አንካሳይቱን ትሩፍ፥ የተጣለችውን ብርቱ መንግሥት አደርጋታለሁ፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘለዓለም በጽዮን ተራራ ጌታ በእነርሱ ላይ ይነግሣል።
8አንተ የመንጋው ግንብ ሆይ፥ የጽዮን ሴት ልጅ ምሽግ ሆይ፥ የቀደመችው ግዛት፥ የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ መንግሥት ወደ አንተ ትገባለች።
9አሁንስ ለምን ጮክ ብልሽ ታለቅሻለሽ? በአንቺ ዘንድ ንጉሥ ስለ ሌለ ነውን? እንደምትወልድ ሴት ምጥ የያዘሽ፥ መካሪሽ ስለ ጠፋ ነውን?
10የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እንደምትወልድ ሴት አምጪ፥ ተጨነቂ፤ አሁን ከከተማ ወጥተሽ በሜዳ ትቀመጫለሽና፥ ወደ ባቢሎንም ትሄጃለሽ፤ በዚያ ትድኛለሽ፥ በዚያም ጌታ ከጠላቶችሽ እጅ ይቤዥሻል።
11አሁንም፦ “ትርከስ፥ ዓይናችን በጽዮን ላይ ይሁን” የሚሉ ብዙ አሕዛብ በአንቺ ላይ ተሰብስበዋል።
12ነገር ግን የጌታን አሳብ አያውቁም፥ ምክሩንም አያስተውሉም፤ እንደ ነዶ በአውድማ አከማችቷቸዋልና።
13የጽዮን ልጅ ሆይ ተነሺ አሂጂ፥ ቀንድሽን ብረት፥ ኮቴሽንም ናስ አደርጋለሁና፤ ብዙ ሕዝቦችን ታደቅቂአለሽ፤ እኔም ትርፋቸውን ለጌታ፥ ሀብታቸውንም ለምድር ሁሉ ጌታ አውለዋለሁ።
14አሁንም የወታደሮች ሴት ልጅ ሆይ፥ ወታደሮችን ትሰበስቢያለሽ፥ በእኛ ላይ ከበባ አድርገዋል፤ የእስራኤልን ፈራጅ ጉንጩን በበትር ይመታሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሚክያስ 4: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ