የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 28

28
የኢየሱስ ከሙታን መነሣት
(ማር. 16፥1-8ሉቃ. 24፥1-12ዮሐ. 20፥1-10)
1በሰንበት መጨረሻ ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሌላይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ። 2እነሆ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ መጥቶም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። 3መልኩ እንደ መብረቅ፥ ልብሱ ደግሞ እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። 4እርሱን ከመፍራት የተነሣ ጠባቂዎቹ ተንቀጠቀጡ፤ እንደ ሞተ ሰው ሆኑ። 5መልአኩም ሴቶቹን እንዲህ አላቸው “አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ አውቃለሁና፤ 6በዚህ የለም፤ እንደ ተናገረው ተነሥቶአልና፤ ተኝቶ የነበረበትን ስፍራ ኑና እዩ። 7ፈጥናችሁ ሂዱና ‘ከሙታን ተነሥቶአል፤ እነሆ ወደ ገሊላ ቀድሞአችሁ ይሄዳል፤ በዚያም ታዩታላችሁ’ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው። እነሆ ነግሬአችኋለሁ።” 8በፍርሃትና በታላቅ ደስታ ፈጥነው ከመቃብሩ ሄዱ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሊነግሩ ሮጡ። 9እነሆ ኢየሱስ አገኛቸውና “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። 10በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “አትፍሩ፤ ሄዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሩአቸው፤ በዚያም ያዩኛል” አላቸው።
11ሲሄዱም ሳሉ እነሆ ከጠባቂዎቹ አንዳንዶቹ ወደ ከተማ መጥተው የሆነውን ሁሉ ለሊቃነ ካህናቱ አወሩ። 12ከሽማግሌዎች ጋር ተሰብስበው ተማከሩና ለወታደሮቹ ብዙ ገንዘብ ሰጡአቸው፥ 13እንዲህም አሉአቸው፦ “‘እኛ ተኝተን ሳለን ደቀመዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት’ በሉ። 14ይህም በገዢው ዘንድ የተሰማ እንደሆነ፥ እኛ እናሳምነዋለን፤ እናንተም ከሥጋት ነጻ እንድትሆኑ እናደርጋለን።” 15እነርሱም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ አስተማሩአቸው አደረጉ። ይህም ነገር በአይሁድ ዘንድ እስከ ዛሬ ድረስ ይወራል።
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲያስተምሩ እንዳዘዛቸው
(ማር. 16፥14-18ሉቃ. 24፥36-49ዮሐ. 20፥19-23የሐዋ. 1፥6-8)
16 # ማቴ. 26፥32፤ ማር. 14፥28። ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፤ 17ባዩትም ጊዜ ሰገዱ፤ አንዳዶቹ ግን ተጠራጠሩ። 18ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ አላቸው “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል። 19#የሐዋ. 1፥8።ስለዚህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፥ በወልድና መንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ 20ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሩአቸው፤ እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮዎች ለየማቴዎስ ወንጌል 28