ኢየሱስ በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም “አንተ አልህ” አለው። በሊቃነ ካህናትና በሽማግሌዎች ሲከሰስ ምንም አልመለሰም። በዚያን ጊዜ ጲላጦስ “ስንት ነገር እንደሚመሰክሩብህ አትሰማምን?” አለው። እርሱ ግን አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰለትም፤ በዚህም ገዢው እጅግ ተደነቀ። በዚያ በዓል፥ ገዢው ሕዝቡ የወደደውን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው። በዚያን ጊዜ በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው። ስለዚህ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ “ማንን ልፍታላችሁ ኢየሱስ በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን?” አላቸው። በቅናት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ፥ ሚስቱ “በእርሱ ምክንያት ዛሬ በሕልም ብዙ ተሠቃይቻለሁና በዚያ ጻድቅ ላይ ምንም እንዳታደርግ” ስትል ላከችበት። ሊቃነ ካህናቱና ሽማግሌዎቹ ግን በርባን እንዲለቀቅ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፋ ሕዝቡን አግባቡ። ገዢውም መልሶ “ከሁለቱ የትኛውን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው፤ እነርሱም “በርባንን” አሉ። ጲላጦስም “ታዲያ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ምን ላድርገው?” አላቸው፤ ሁሉም “ይሰቀል!” አሉ። እርሱም “ምን ክፉ ነገር ሠራና?” አለ፤ እነርሱ ግን “ይሰቀል!” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ጲላጦስም ይህ ነገር ሁከት ከማስነሳት በስተቀር ምንም እንደማይጠቅም ባየ ጊዜ፥ ውሃ ወስዶ “እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ ጉዳዩ የእናንተ ነው፤” ብሎ በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። ሕዝቡም ሁሉ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” ብለው መለሱ። በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። በዚያን ጊዜ የገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ውስጥ ወሰዱት፤ ጭፍራውንም ሁሉ ወደ እርሱ ሰበሰቡ። ልብሱንም ገፈው ቀይ ካባ አለበሱት፤ የእሾህ አክሊል ጐንጉነው በራሱ ላይ፥ በቀኝ እጁም መቃ አኖሩ፤ በፊቱም ተንበርክከው “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን” እያሉ አፌዙበት፤ ተፉበት፤ መቃውንም ነጥቀው ራሱን መቱት። ከአፌዙበትም በኋላ ካባውን ገፈው የራሱን ልብስ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። ሲወጡም ስምዖን የሚባል የቀሬና ሰው አገኙ፤ መስቀሉንም እንዲሸከም አስገደዱት። ትርጉሙ የራስ ቅል ስፍራ ወደሚባል ጎልጎታ ወደ ተባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልፈለገም። ከሰቀሉትም በኋላ ልብሶቹን ዕጣ ጥለው ተካፈሉት፤ በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። የተከሰሰበትንም ምክንያት “ይህ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍ ከራሱ በላይ አኖሩ። በዚያን ጊዜ ከእርሱ ጋር ሁለት ወንበዴዎች አንዱ በቀኙ አንዱ ደግሞ በግራው ተሰቀሉ። በዚያ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበር፤ “ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራው፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህሰ እስቲ ከመስቀል ውረድ፤” ይሉት ነበር። እንዲሁም ደግሞ ሊቃነ ካህናት፥ ከጻፎችና ከሽማግሌዎች ጋር እያፌዙ እንዲህ አሉት፦ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ነው፤ አሁን ከመስቀል ይውረድና እኛም በእርሱ እናምናለን። በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ብሏልና የሚወደው ከሆነ እስቲ አሁን ያድነው።” ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎችም ደግሞ እንዲህ እያሉ ይሰድቡት ነበር። ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ኢየሱስ “ኤሊ ኤሊ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም “አምላኬ አምላኬ፥ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆሙት ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ሰምተው “ኤልያስን ይጠራል” አሉ። ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠና ሰፍነግ ወስዶ የወይን ሆምጣጤ ሞላበት፤ በመቃም አስሮ አጠጣው። የተቀሩት ግን “ተወው፤ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደሆነ እንይ” አሉ። ኢየሱስ እንደገና በታላቅ ድምፅ ጮኾ መንፈሱን ሰጠ። እነሆ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው ከነበሩት የብዙ ቅዱሳን በድን ተነሣ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስቷ ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ። የመቶ አለቃውና ከእርሱም ጋር ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት የምድርን መናወጥና የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው “በእውነት ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” አሉ። ኢየሱስን እያገለገሉት ከገሊላ የተከተሉት፥ በሩቅ ሆነው የሚመለከቱ ብዙ ሴቶች እዚያ ነበሩ፤ ከእነርሱም መግደላዊት ማርያም፥ የያዕቆብና የዮሴፍ እናት ማርያምና የዘብዴዎስ ልጆች እናት ነበሩ። በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የሚባል ሀብታም ሰው ከአርማትያስ መጣ፤ እርሱም የኢየሱስ ደቀመዝሙር ነበረ፤ እርሱም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤ ጲላጦስም እንዲሰጠው አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ወስዶ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፤ ከዐለት በወቀረው በአዲሱ መቃብሩ አኖረው፤ በመቃብሩ በር ላይ ትልቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ።
የማቴዎስ ወንጌል 27 ያንብቡ
ያዳምጡ የማቴዎስ ወንጌል 27
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 27:11-60
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos