በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አገረ ገዥው ፊት ቀረበ፤ አገረ ገዥውም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” በማለት ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አንተው እንዳልኸው ነው” ሲል መለሰለት። የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ሲከስሱት ግን ምንም መልስ አልሰጠም። በዚህ ጊዜ ጲላጦስ፣ “ስንት ነገር አቅርበው እንደሚከስሱህ አትሰማምን?” አለው። እርሱ ግን አገረ ገዥው እስኪገረም ድረስ ለቀረበበት ክስ አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰም። አገረ ገዥው ሕዝቡ በበዓሉ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው። በዚያ ጊዜ በዐመፅ የታወቀ በርባን የሚባል እስረኛ ነበር። ሕዝቡ እንደ ተሰበሰቡ ጲላጦስ፣ “ከበርባንና ክርስቶስ ከሚባለው ከኢየሱስ፣ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው፤ ጲላጦስም በቅናት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፣ “በርሱ ምክንያት ዛሬ በሕልም ብዙ ስለ ተሠቃየሁ፣ በዚያ ንጹሕ ሰው ላይ ምንም ነገር እንዳታደርግ” የሚል መልእክት ላከችበት። ነገር ግን የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች በርባን እንዲፈታላቸው ኢየሱስ ግን እንዲገደል ይለምኑ ዘንድ ሕዝቡን ያግባቡ ነበር። አገረ ገዥውም፣ “ከሁለቱ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” በማለት ጠየቀ። እነርሱም፤ “በርባንን” በማለት መለሱ። ጲላጦስም፣ “ታዲያ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስንስ ምን ላድርገው?” አላቸው። ሁሉም፣ “ይሰቀል!” አሉ። ጲላጦስም፣ “ለምን? ምን ክፉ ነገር አድርጓል?” በማለት ጠየቃቸው። እነርሱ ግን አብዝተው እየጮኹ፣ “ይሰቀል!” አሉ። ጲላጦስ ሁኔታው ሽብር ከማስነሣት በቀር ምንም ፋይዳ የሌለው መሆኑን ተመልክቶ፣ “እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ ከእንግዲህ ኀላፊነቱ የራሳችሁ ነው” በማለት ውሃ አስመጥቶ በሕዝቡ ፊት እጆቹን ታጠበ። ሕዝቡም በሙሉ፣ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን!” ብለው መለሱ። በዚህ ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ካስገረፈው በኋላ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። ከዚያም የአገረ ገዥው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዥው ግቢ ወሰዱት፤ ሰራዊቱንም ሁሉ በዙሪያው አሰባሰቡ። ልብሱን ገፍፈው ቀይ ልብስ አጠለቁለት፤ እሾኽ ጐንጕነው አክሊል በመሥራት ራሱ ላይ ደፉበት፤ የሸንበቆ በትር በቀኝ እጁ በማስያዝ በፊቱ ተንበርክከው፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለት አሾፉበት፤ ተፉበትም፤ የሸንበቆ በትሩን ከእጁ ወስደው ራሱን መቱት፤ ካሾፉበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፍፈው የራሱን ልብስ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ይዘውት ሄዱ። ይዘውትም ሲሄዱ ስምዖን ተብሎ የሚጠራ የቀሬና ሰው አገኙ፤ መስቀሉንም እንዲሸከም አስገደዱት። ትርጕሙ፣ “የራስ ቅል ስፍራ” ከሆነው ጎልጎታ ከተባለው ቦታ ሲደርሱ፣ ከሐሞት ጋራ የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን ቀምሶ ሊጠጣው አልፈቀደም። ከሰቀሉትም በኋላ ዕጣ ጥለው ልብሱን ተካፈሉ፤ በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። ከራስጌውም፣ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ነው” የሚል የክስ ጽሑፍ አኖሩ። ሁለት ወንበዴዎች አንዱ በቀኙ፣ አንዱ በግራው ዐብረውት ተሰቅለው ነበር። በመንገድ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ ይሉት ነበር፤ “አንተ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራ፤ እስኪ ራስህን አድን! የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ!” ይሉት ነበር። የካህናት አለቆችም ከኦሪት ሕግ መምህራንና ከሽማግሌዎች ጋራ ሆነው እያሾፉበት እንዲህ ይሉ ነበር፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እናምንበታለን። በእግዚአብሔር ታምኗል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ይል ስለ ነበር እስኪ ከወደደው አሁን ያድነው!” ከርሱ ጋራ የተሰቀሉት ወንበዴዎችም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር። ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝ ሰዓት ገደማ፣ ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” እያለ ጮኸ፤ ትርጕሙም “አምላኬ፤ አምላኬ፤ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ጩኸቱን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን እየተጣራ ነው!” አሉ። ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጦ ሰፍነግ በመውሰድ የኮመጠጠ ወይን ጠጅ ውስጥ ነከረው፤ ሰፍነጉንም በሸንበቆ ዘንግ ጫፍ ላይ በማድረግ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት። የቀሩት ግን፣ “ተዉት፤ እስኪ ኤልያስ መጥቶ ሲያድነው እናያለን!” አሉ። ኢየሱስ እንደ ገና ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ፤ መንፈሱንም አሳልፎ ሰጠ። በዚያ ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፤ ምድር ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጣጠቁ፤ መቃብሮች ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው የነበሩትም ብዙዎች ቅዱሳን ተነሡ፤ ከመቃብርም በመውጣት ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ገብተው ለብዙዎች ታዩ። የመቶ አለቃውና ዐብረውት ኢየሱስን ይጠብቁት የነበሩት የመሬት መናወጡንና የሆነውን ነገር ሁሉ ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው፣ “ይህስ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር!” አሉ። ከገሊላ የመጡና ኢየሱስን በሚያስፈልገው ነገር ለማገልገል የተከተሉት ብዙ ሴቶች ሁኔታውን ከርቀት እየተመለከቱ በአካባቢው ነበሩ። ከእነርሱም መካከል ማርያም መግደላዊት፣ ማርያም የያዕቆብና የዮሴፍ እናት እንዲሁም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ነበሩ። ምሽት ላይ ዮሴፍ የሚባል ሀብታም ሰው ከአርማትያስ መጣ፤ እርሱ ራሱም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ። ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤ ጲላጦስም እንዲሰጠው አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ወስዶ በንጹሕ የበፍታ ጨርቅ ከፈነው፤ ለራሱ ከዐለት አስፈልፍሎ ባዘጋጀው መቃብር ውስጥ አኖረው፤ ከዚያም ትልቅ ድንጋይ አንከባልሎ የመቃብሩን በር ዘግቶ ሄደ።
ማቴዎስ 27 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 27
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 27:11-60
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos