የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 26:30-46

የማቴዎስ ወንጌል 26:30-46 መቅካእኤ

መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረዘይት ወጡ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ተጽፎአልና፥ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” ጴጥሮስም “ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እንኳ እኔ ከቶ አልሰናከልም” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስም “ከአንተ ጋር መሞት ቢያስፈልግ እንኳ፥ ከቶ አልክድህም፤” አለው። ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ እንደዚሁ አሉ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱንም “ወደዚያ ሄጄ እስክጸልይ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው። ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች ይዞ ሄደና ማዘንና መጨነቅ ጀመረ። “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች፤ እዚህ ቆዩ፤ ከእኔም ጋር ትጉ” አላቸው። ወደ ፊት ጥቂት እልፍ ብሎ በፊቱ ተደፋና እንዲህ ሲል ጸለየ “አባቴ! የሚቻል ከሆነ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን እንደ አንተ ፈቃድ እንጂ እንደ እኔ አይሁን።” ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ መትጋት አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፥ ጸልዩም፤ መንፈስ በእርግጥ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ሄዶ “አባቴ ሆይ! ይህንን ሳልጠጣው ሊያልፍ የማይቻል ከሆነ፥ ፈቃድህ ይሁን” ብሎ ጸለየ። ዳግመኛ ሲመጣ ተኝተው አገኛቸው፥ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና። እንደገና ትቶአቸው ሄደ፤ ያንኑ ቃል ለሦስተኛ ጊዜ ደግሞ ጸለየ። ከዚህ በኋላ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጥቶ እንዲህ አላቸው “ከእንግዲህስ ተኙ፥ ዕረፉም፤ እነሆ ሰዓቱ ቀርቦአል፤ የሰው ልጅም በኀጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል። ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች