የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 26:30-46

የማቴዎስ ወንጌል 26:30-46 አማ05

ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፥ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ተጽፎአልና በዚህች ሌሊት፥ ሁላችሁም ትክዱኛላችሁ። ነገር ግን ከሞት ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ፥ “ሌሎቹ ሁሉ እንኳ ቢክዱህ እኔ ከቶ አልክድህም!” ብሎ ተናገረ። ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚህች ሌሊት ዶሮ ከመጮሁ በፊት አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስ ግን “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልግ ቢሆን እሞታለሁ እንጂ ከቶ አልክድህም!” አለው። የቀሩትም ደቀ መዛሙርት ሁሉ እንዲሁ ይሉ ነበር። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሱ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “እኔ እዚያ ሄጄ እስክጸልይ እናንተ እዚህ ቈዩ” አላቸው። ከእርሱ ጋር ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች አስከትሎ ሄደ፤ ያዝንና ይጨነቅም ጀመረ። እንዲህም አላቸው፦ “ለመሞት እስክደርስ ድረስ አዝኛለሁ፤ እናንተ እዚህ ቈዩ፤ ከእኔም ጋር ንቁ።” ከእነርሱ ጥቂት ራቅ ብሎ ሄደና፥ በመሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ፥ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “አባት ሆይ! የሚቻል ከሆነ ይህ የመከራ ጽዋ ከእኔ ወዲያ ይለፍ! ነገር ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።” ከዚህ በኋላ ወደ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተመልሶ በመጣ ጊዜ ተኝተው አገኛቸው፤ ስለዚህ፥ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር ለአንዲት ሰዓት እንኳ መንቃት አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ በእርግጥ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደገናም ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ ርቆ ሄደና “አባቴ ሆይ! ይህ የመከራ ጽዋ ሳልጠጣው ሊያልፍ የማይቻል ከሆነ የአንተ ፈቃድ ይሁን” ሲል ጸለየ። ደግሞም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ በመጣ ጊዜ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። እንደገናም ትቶአቸው ሄደና ያንኑ የፊተኛውን ቃል በመናገር ሦስተኛ ጊዜ ጸለየ። ከዚህ በኋላ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ መጣና እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም ገና ተኝታችኋልን? ዕረፍትም እያደረጋችሁ ነውን? እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ የሚሰጥበት ሰዓቱ ደርሶአል፤ ተነሡ እንሂድ! እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል!”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች