የማቴዎስ ወንጌል 25:14-40

የማቴዎስ ወንጌል 25:14-40 መቅካእኤ

“እንግዲህ ወደ ሌላ አገር ሊሄድ ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት እንደሰጣቸው ሰው ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው፥ ለአንዱ አምስት መክሊት፥ ለአንዱ ሁለት፥ ለአንዱ ደግሞ አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ወደ ሌላ አገር ሄደ። አምስት መክሊት የተቀበለውም ሄዶ ነገደበትና ሌላ አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄደና ምድርን ቆፍሮ የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ጊዜ በኋላ የእነዚያ ባርያዎች ጌታ መጥቶ ከእነርሱ ጋር መተሳሰብ ጀመረ። አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አምጥቶ ‘ጌታ ሆይ! አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁ’ አለ። ጌታውም ‘መልካም፥ አንተ መልካምና ታማኝ አገልጋይ፥ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። ባለ ሁለት መክሊቱም ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁ’ አለ። ጌታውም ‘መልካም፥ አንተ መልካምና ታማኝ አገልጋይ፥ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። አንድ መክሊት የተቀበለውም ደግሞ ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደሆንህ አውቃለሁ፤ ስለፈራሁም ሄጄ መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ የራስህ ይኸውልህ’ አለ። ጌታውም እንዲህ ሲል መለሰለት ‘አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባርያ፥ ካልዘራሁበት እንደማጭድ ካልበተንሁበትም እንደምሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለገንዘብ ለዋጮች መስጠት ነበረብህ፤ እኔም በመጣሁ ጊዜ ያለኝን ከነወለዱ እወስደው ነበር። በሉ እንግዲህ መክሊቱን ውሰዱበትና ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፤ ይበዛለታልም፤ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። የማይረባውን ባርያ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።’ “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ፥ ያንጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብ ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፤ በጎቹን በቀኙ ፍየሎቹን ደግሞ በግራው ያቆማቸዋል። ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል ‘እናንተ የአባቴ ቡሩካን! ኑ! ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፤ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል፤ ታርዤ አልብሳችሁኛል፤ታምሜ ጠይቃችሁኛል፤ ታስሬ ጠይቃችሁኛል።’ ጻድቃኑም እንዲህ ሲሉ ይመልሱለታል ‘ጌታ ሆይ! መቼ ተርበህ አየንህና አበላንህ? መቼ ተጠምተህ አየንህና አጠጣንህ? መቼ እንግዳ ሆነህ አየንህና ተቀበልንህ? መቼ ታርዘህ አየንህና አለበስንህ? መቼ ታመህ ወይም ታስረህ አየንህና ወደ አንተ መጥተን ጠየቅንህ?’ ንጉሡም እንዲህ ሲል ይመልስላቸዋል ‘እውነት እላችኋለሁ፤ ከሁሉ ለሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው።’

ተዛማጅ ቪዲዮዎች