የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 25:14-40

ማቴዎስ 25:14-40 NASV

“የእግዚአብሔር መንግሥት ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት በዐደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሊሄድ የተነሣ አንድ ሰውን ትመስላለች፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ ዐምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጥቶ ጕዞውን ቀጠለ። ዐምስት ታላንት የተቀበለው ሰው፣ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ ዐምስት ታላንት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤ አንድ ታላንት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ። “የባሪያዎቹም ጌታ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከሄደበት ተመልሶ የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ። ዐምስት ታላንት የተቀበለውም፣ ሌላ ዐምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ዐምስት ታላንት ዐደራ ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸውልህ ዐምስት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው። “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ ባሪያ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። “እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሁለት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው። “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ ባሪያ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። “አንድ ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ ፈራሁህ፤ ሄጄም መሬት ቈፍሬ ታላንትህን ጕድጓድ ውስጥ ደበቅሁት፤ ገንዘብህ ይኸውልህ’ አለው። “ጌታውም መልሶ፣ ‘አንተ ክፉ፣ ሰነፍ ባሪያ፤ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሯል? ታዲያ፣ በምመለስበት ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እንዳገኘው ለለዋጮች መስጠት ይገባህ ነበር። “ ‘በሉ እንግዲህ ታላንቱን ወስዳችሁ ዐሥር ታላንት ላለው ስጡ፤ ላለው ይጨመርለታል፤ ይትረፈረፍለታልም፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ይህን የማይረባ ባሪያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት’ አለ። “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋራ በክብሩ ሲመጣ፣ በክብሩ ዙፋን ላይ ይቀመጣል፤ ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እርሱም፣ እረኛ በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ፣ ሕዝቡን አንዱን ከሌላው ይለያል፤ በጎቹን በቀኙ፣ ፍየሎቹን ግን በግራው ያቆማቸዋል። “በዚያ ጊዜ ንጉሡ በቀኙ በኩል ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፤ ‘እናንተ አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ፤ ምክንያቱም ተርቤ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፤ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል፤ ታርዤ አልብሳችሁኛል፤ ታምሜ አስታምማችሁኛል፤ ታስሬ ጠይቃችሁኛል።’ “ጻድቃንም መልሰው እንዲህ ይሉታል፤ ‘ጌታ ሆይ፤ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህ? ወይም ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? እንዲሁም ታምመህ ወይም ታስረህ አይተን መቼ ጠየቅንህ?’ “ንጉሡም መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት፣ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው’ ይላቸዋል።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች