የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 12:22-50

የማቴዎስ ወንጌል 12:22-50 መቅካእኤ

ከዚህ በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውርና ዲዳ ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም ፈወሰው፤ ዲዳውም ተናገረ አየም። ሕዝቡም ሁሉ ተገርመው “ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ። ፈሪሳውያን ግን ይህን ሰምተው “ይህ በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ካልሆነ በስተቀር አጋንንትን አያወጣም” አሉ። እርሱ ግን ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው “እርስ በርስዋ የምትከፋፈል መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፤ እርስ በርስዋ የምትከፋፈል ከተማ ወይም ቤት ሁላ አትቆምም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ ማለት ነው፤ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት መቆም ይችላል? እኔ አጋንንትን በብዔልዜቡል የማስወጣ ከሆነ፥ ልጆቻችሁ በማን ያስወጡአቸዋል? በዚህም ምክንያት እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማስወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መጥታለች። ወይስ አንድ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ንብረቱን እንዴት መዝረፍ ይችላል? ካሰረው በኋላ ግን ቤቱን ይዘርፋል። ከእኔ ጋር ያልሆነ ተቃዋሚዬ ነው፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብ ደግሞ ይበትናል። በዚህም ምክንያት እላችኋለሁ፤ ሰው ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስን የሰደበ ግን አይሰረይለትም። በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ ግን በዚህ ዓለምም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም። “ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፤ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ፤ ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ነገር ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ የሞላውን አፍ ይናገራልና። መልካም ሰው ከመልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህ፥ ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህና።” በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና “መምህር ሆይ! ከአንተ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁም የሰው ልጅ በምድር ልብ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይቆያል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፤ እነሆ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ። የደቡብ ንግሥት በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና፤ እነሆ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ። “ርኩስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት ፍለጋ ውሃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፤ አያገኝምም። በዚያን ጊዜ ‘ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ’ ይላል፤ ሲመጣም ባዶ ሆኖ፥ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል። ከዚያ ይሄድና ከእርሱ የከፉ ሰባት ሌሎች አጋንንትን ከእርሱ ጋር ይዞ ይመጣል፤ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ የሰውየው መጨረሻ ከፊተኛው ይልቅ የከፋ ይሆናል። ለዚህም ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል።” ለሕዝቡ ይህን እየተናገረ ሳለ፥ እነሆ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊነጋገሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። አንድ ሰውም “እነሆ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው። እርሱ ግን ለነገረው መልሶ እንዲህ አለው “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አለው። እጁንም ወደ ደቀመዛሙርቱ ዘርግቶ “እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ፥ እኅቴም እናቴም ነውና።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች

Free Reading Plans and Devotionals related to የማቴዎስ ወንጌል 12:22-50