የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 4:14-30

የሉቃስ ወንጌል 4:14-30 መቅካእኤ

ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለው አገር ሁሉ ተወራ። እንዲሁም በሁሉም እየተመሰገነ በምኵራባቸው ያስተምር ነበር። ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደተለመደው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሣ። የነቢዩም የኢሳይያስ ጥቅል ብራና ተሰጠው፤ ጥቅሉንም በዘረጋው ጊዜ፥ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ፤ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች መልካም ዜናን እንዳበሥር ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዐይነ ስውሮችም ማየትን እንዳውጅ፥ የተጨቆኑትንም ነጻ እንዳወጣ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል።” ጥቅል ብራናውንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ መልሶ ከሰጠ በኋላ ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኩር ብለው ይመለከቱት ነበር። እርሱም፦ “ዛሬ ይህ በጆሮዎቻችሁ የሰማችሁት ጽሑፍ ተፈጸመ፤” ይላቸው ጀመር። ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር፤ ከአፉም ከሚወጡት ቃላት ጸጋ የተነሣ እየተደነቁ፦ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይሉ ነበር። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ያለ ምንም ጥርጥር ይህንን ምሳሌ ትጠቅሱብኛላችሁ ‘አንተ ሐኪም! እስቲ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም እንዳደረግህ የሰማናቸውን ነገሮች ሁሉ፥ በዚህ በገዛ አገርህ ደግሞ አድርግ።’ ” እንዲህም አለ፦ “እውነት እላችኋለሁ፤ አንድም ነቢይ በገዛ አገሩ ተቀባይነት የለውም። ነገር ግን በእውነት እላችኋለሁ፤ በኤልያስ ዘመን ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ተዘግቶ ሳለ፥ በምድር ሁሉ ላይ ብርቱ ራብ በነበረ ጊዜ፥ በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ፤ ቢሆንም ግን ኤልያስ ወደ ሲዶናዊቷ መበለት ወደ ሰራፕታ እንጂ ወደ ሌሎቹ ወደ አንዳቸውም አልተላከም። በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፤ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነርሱ ማንም አልነጻም።” በምኵራብም ውስጥ የነበሩ ሁሉ እነዚህን ነገሮች በሰሙ ጊዜ በቁጣ ተሞሉ፤ ተነሥተውም ከከተማይቱ ውጭ አወጡት፤ ገፍትረውም ሊጥሉት ከተማቸው ተሠርታባት ወደ ነበረች ኮረብታ አፋፍ ላይ ወሰዱት፤ እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ።