“ለሕዝቡም የሆነውን የኃጢአት መሥዋዕት ፍየል ያርዳል፥ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ያመጣዋል፤ በወይፈኑም ደም እንዳደረገ እንዲሁ በፍየሉ ደም ላይ ያደርጋል፤ በስርየቱ መክደኛም ላይና በስርየቱ መክደኛም ፊት ለፈት ይረጨዋል። ከእስራኤል ልጆች ርኩስነት፥ ከመተላለፋቸውም፥ ከኃጢአታቸውም ሁሉ የተነሣ ለተቀደሰው ስፍራ ያስተሰርይለታል፤ በርኩስነታቸውም መካከል ከእነርሱ ጋር ላለው ለመገናኛው ድንኳን እንዲሁ ያደርጋል። አሮንም ለማስተስረይ ወደተቀደሰው ስፍራ በገባ ጊዜ ለራሱ፥ ለቤተሰቡም፥ ለእስራኤል ጉባዔ ሁሉ አስተስርዮ እስኪ ወጣ ድረስ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ማንም ሰው አይገኝ። ከዚያም በኋላ በጌታ ፊት ወዳለው ወደ መሠዊያው ይወጣል፤ ለእርሱም ያስተሰርይለታል፤ ከወይፈኑም ደም ከፍየሉም ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን ቀንዶች ያስነካል። ከደሙም በእርሱ ላይ ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል፥ ከእስራኤልም ልጆች ርኩስነት ያነጻዋል፥ ይቀድሰዋልም። “የተቀደሰውንም ስፍራ፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ መሠዊያውንም ማስተስረይ ከፈጸመ በኋላ በሕይወት ያለውን ፍየል ያቀርባል፤ አሮንም ሁለቱን እጆቹን በሕይወት ባለው ፍየል ራስ ላይ ይጭናል፥ በላዩም የእስራኤልን ልጆች በደል ሁሉ፥ መተላለፋቸውንም ሁሉ፥ ኃጢአታቸውንም ሁሉ ይናዘዛል፤ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል፥ በተዘጋጀው ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ እንዲሄድ ያደርገዋል። ፍየሉም በደላቸውን ሁሉ በረሀ ወደ ሆነ ስፍራ ይሸከማል፤ ፍየሉንም በምድረ በዳ ውስጥ እንዲሄድ ይለቅቀዋል። “አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባል፥ ወደ ተቀደሰውም ስፍራ በገባ ጊዜ የለበሰውን የበፍታ ልብስ ያወልቃል፥ በዚያም ይተወዋል፤ በተቀደሰውም ስፍራ ገላውን በውኃ ይታጠባል፥ ሌላውንም ልብስ ይለብሳል፤ ወጥቶም ለእርሱ የሆነውን የሚቃጠል መሥዋዕት እና ለሕዝቡ የሆነውን የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፥ ለራሱም ለሕዝቡም ያስተሰርያል። የኃጢአቱንም መሥዋዕት ስብ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ወደ ዐዛዜል የሄደውን ፍየል የወሰደው ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል። ለማስተስረያም እንዲሆን ደማቸው ወደተቀደሰው ስፍራ የገባውን፥ የኃጢአቱን መሥዋዕት ወይፈንና የኃጢአቱን መሥዋዕት ፍየል ከሰፈሩ ውጭ ያወጡአቸዋል፤ ቆዳቸውንም፥ ሥጋቸውንም፥ ፈርሳቸውንም በእሳት ያቃጥላሉ። ያቃጠላቸውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል። “ይህም የዘለዓለም ሥርዓት ይሁንላችሁ፤ በሰባተኛው ወር ከወሩም በአስረኛው ቀን ራሳችሁን አዋርዱ፥ የአገሩም ተወላጅ ሆነ በእናንተ መካከል የተቀመጠም እንግዳ ሥራን ሁሉ አትሥሩበት፤ ለእናንተ በዚህ ቀን እንድትነጹ ማስተስረያ ይደረግላችኋልና፤ በጌታም ፊት ከኃጢአታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ። ለእናንተም ፈጽሞ የምታርፉበት ታላቅ ሰንበት ይሆናል፥ ራሳችሁንም ታዋርዳላችሁ፤ የዘለዓለም ሥርዓት ነው። በአባቱም ፈንታ ካህን ሆኖ ለማገልገል ተለይቶ የሚቀባው ካህን የተቀደሰውን የበፍታ ልብስ ለብሶ ያስተስርያል። ለቅድስተ ቅዱሳንም ያስተስርይ፤ ለመገናኛውም ድንኳን ለመሠዊያውም ያስተስርይ፤ ለካህናቱም ለጉባኤውም ሕዝብ ሁሉ ያስተስርይ። ይህም አንድ ጊዜ በዓመት ለእስራኤል ልጆች ስለ ኃጢአታቸው ሁሉ ለማስተሰረይ የዘለዓለም ሥርዓት ይሆንላችኋል።” ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረገ።
ኦሪት ዘሌዋውያን 16 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 16:15-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች