ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “እኔ ወደምሰጣችሁ ርስት ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ በምትወርሱአት ምድር በአንድ ቤት ውስጥ የለምጽ ደዌ ባኖር፥ የቤቱ ባለቤት መጥቶ ካህኑን፦ ‘ደዌ የሚመስል ነገር በቤቴ ውስጥ ያለ ይመስለኛል’ ብሎ ይንገረው። ካህኑም በቤቱ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ እንዳይረክስ፥ እርሱ ደዌውን ለማየት ወደ ቤቱ ከመግባቱ በፊት፥ ቤቱን ባዶ እንዲያደርጉት ያዝዛል፤ ከዚያም በኋላ ካህኑ ቤቱን ለማየት ይገባል። ደዌውንም ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ግድግዳ ላይ አረንጓዴ ወይም ቀይ ሆኖ ቢዥጐረጐር፥ መልኩም ከግድግዳው ውጫዊ ገጽታ ዘልቆ ቢገባ፥ ካህኑ ከቤቱ ውስጥ ወደ ቤቱ በር ወጥቶ ሰባት ቀን ቤቱን ይዘጋዋል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ተመልሶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ግድግዳ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ ደዌ ያለባቸውን ድንጋዮች እንዲያወጡ፥ ከከተማውም ውጭ ወደ ረከሰው ስፍራ እንዲጥሉአቸው ያዝዛል። የቤቱንም ውስጥ ዙሪያውን ያስፍቀዋል፤ የፋቁትንም የምርጊቱን አፈር ከከተማው ውጭ ወደ ረከሰ ስፍራ ያፈስሱታል። በእነዚያም ድንጋዮች ስፍራ ሌሌች ድንጋዮችን አምጥተው ያገባሉ፤ ሌላም ጭቃ ወስደው ቤቱን ይመርጉታል። “ደዌውም ዳግም ቢመለስ፥ ድንጋዮቹም ከወጡ ቤቱም ከተፋቀና ከተመረገ በኋላ በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ፥ ካህኑ ገብቶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ውስት ቢሰፋ፥ በቤቱ ውስጥ ያለው እየሰፋ የሚሄድ የለምጽ ደዌ ነው፤ እርሱ ርኩስ ነው። ቤቱንም፥ ድንጋዮቹንም፥ እንጨቱንም፥ የቤቱንም ምርጊት ሁሉ ያፈርሳል፤ እነርሱንም ከከተማው ውጭ ወደ ርኩስ ስፍራ ያወጣል። በተዘጋበትም ጊዜ ሁሉ ወደ ቤቱ የሚገባ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። በቤቱም ውስጥ የሚተኛ ልብሱን ያጥባል፤ በቤቱም ውስጥ የሚበላ ልብሱን ያጥባል። “ካህኑም ገብቶ ቢያይ፥ እነሆም፥ ቤቱ ከተመረገ በኋላ ደዌው በቤቱ ውስጥ ባይሰፋ፥ ደዌው ስለ ጠፋ ካህኑ ቤቱን፦ ንጹሕ ነው ይለዋል። ቤቱንም ለማንጻት ሁለት ወፎች፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም ይወስዳል። አንደኛውንም ወፍ በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ ያርዳል። የዝግባውን እንጨት፥ ሂሶጱንም፥ ቀዩንም ግምጃ፥ በሕይወትም ያለውን ወፍ ወስዶ በታረደው ወፍ ደምና በምንጩ ውኃ ውስጥ ይነክራቸዋል፥ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። ቤቱንም በወፉ ደም፥ በምንጩም ውኃ፥ ሕይወትም ባለው ወፍ፥ በዝግባውም እንጨት፥ በሂሶጱም፥ በቀዩም ግምጃ ያነጻዋል። በሕይወትም ያለውን ወፍ ከከተማ ወጥቶ ወደ ተንጣለለው ሜዳ እንዲበር ይለቀዋል፤ ለቤቱም ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ንጹሕ ይሆናል።” “ይህ ሕግ ለሁሉም ዓይነት የለምጽ ደዌ፥ ለቈረቈርም፥ በልብስ ላይና በቤት ውስጥ ላለ የለምጽ ደዌ፥ ለእባጭም፥ ለብጉርም፥ ለቋቁቻም የሚሆን ነው። እንዲሁም አንድ ነገር በሚረክስና በሚነጻ ጊዜ ለማልከት የሚያስችል ነው። ይህ የለምጽ ደዌ ሕግ ነው።”
ኦሪት ዘሌዋውያን 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 14:33-57
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች