የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 6

6
1ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦
2“ትካዜዬ ምነው በተመዘነ!
መከራዬም በሚዛን ላይ ምነው በተቀመጠ!
3ከባሕር አሸዋ ይልቅ በከበደ ነበርና፥
ለዚህም ነው ቃሌ ደፋር የሆነው።
4ሁሉን የሚችል የአምላክ ፍላጻ በሥጋዬ ውስጥ ነው፥
መርዙንም ነፍሴ ትጠጣለች፥
የእግዚአብሔር ሽብሮች በኔ ላይ ተሰልፈዋል።
5በውኑ የሜዳ አህያ ሣር እያለው ይጮኻልን?
ወይስ በሬ ገለባ እያለው ይጮኻልን?
6የማይጣፍጥስ ነገር ያለ ጨው ይበላልን?
ወይስ የእንቁላል ውኃ ይጥማልን?
7ሰውነቴ ትነካው ዘንድ እንቢ አለችው፥
እንደሚያስጸይፍ መብል ሆነብኝ።
8ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ!
እግዚአብሔርም ምኞቴን ምነው በሰጠኝ!
9እግዚአብሔርም ያደቀኝ ዘንድ፥
እጁንም ለቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ ወድዶ ቢሆን ኖሮ!
10መጽናናት በሆነልኝ ነበር፥
በማይራራ ሕመም ሐሤት ባደረግሁ ነበር፥
የቅዱሱን ቃል አልካድሁምና።
11እጠብቅ ዘንድ ጉልበቴ ምንድነው?
እታገሥም ዘንድ ፍጻሜዬ ምንድነው?
12ጉልበቴ የድንጋይ ጉልበት ነውን?
ሥጋዬስ ነሐስ ነውን?
13በውኑ ረድኤት በእኔ እንደሌለ
ጥበብም ሁሉ ከእኔ ዘንድ እንደ ተባረረ አይደለምን?”
14“ቸርነትን ለወዳጁ የሚነፍግ፥
ሁሉን ቻይ አምላክን መፍራት የተወ ነው።
15ወንድሞቼ እንደ ፈፋ፥
እንደሚያልፍ ፈፋ ሐሰተኞች ሆኑብኝ።
16ከበረዶ የተነሣ ደፈረሱ፥
አመዳይም ተሰወረባቸው፥
17ፀሐይ በተኰሰች ጊዜ ይደርቃሉ፥
በሙቀትም ጊዜ ከስፍራቸው ይጠፋሉ።
18በየዳርቻቸውም የሚሄዱ ነጋዴዎች ፈቀቅ ይላሉ፥
ወደ በረሃ ወጥተው ይጠፋሉ።
19የቴማን#6፥19 የቦታ ስም፥ ኢሳ 21፥ 14ን እና ኤር 25፥23ን ይመልከቱ። ነጋዴዎች ተመለከቱ፥
የሳባ መንገደኞችም ተጠባበቁአቸው።
20ተስፋ አድርገውባቸው ነበርና አፈሩ፥
ወደዚያ ደረሱ፥ እፍረትም ያዛቸው።
21አሁንም እናንተ እንደዚሁ ሆናችኋል፥
መከራዬን አይታችሁ ፈራችሁ።
22በውኑ፦ አንዳች ነገር አምጡልኝ፥
ወይስ፦ ከብልጽግናችሁ ስጦታ አቅርቡልኝ፥
23ወይስ፦ ከጠላቴ እጅ አስጥሉኝ፥
ወይስ፦ ከአስጨናቂው እጅ አድኑኝ አልኋችሁን?
24አስተምሩኝ፥ እኔም ዝም እላለሁ፥
የተሳሳትሁትንም ንገሩኝ።
25የቅንነት ቃል እንዴት ኃይለኛ ነው!
የእናንተ ሙግት ግን ምን ይገሥጻል?
26ተስፋ የሌለው ሰው ንግግር እንደ ነፋስ ነውና
ቃሌን ትገሥጹ ዘንድ ታስባላችሁን?
27በድሀ አደጉ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፥
ለወዳጆቻችሁም ጉድጓድ ትቈፍራላችሁ።
28አሁንም፥ እባካችሁ፥ ወደ እኔ ተመልከቱ፥
በፊታችሁም ሐሰት አልናገርም።
29እባካችሁ፥ ተመለሱ፥ በደል አይሁን፥
ጽድቄ በዚህ ነገር ነውና አንድ ጊዜ ተመለሱ።
30በውኑ በአንደበቴ በደል ይገኛልን?
ምላሴ የተንኰልን ቃና መለየት አይችልምን?”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ