የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 3

3
1 # ኤር. 20፥14-18። ከዚያም በኋላ ኢዮብ መናገር ጀመረ፤ የተወለደበትንም ቀን ረገመ። 2#ሲራ. 23፥14።ኢዮብም እንዲል ሲል ተናገረ፦
3“ያ የተወለድሁበት ቀን ይጥፋ፥
እንዲሁም፦ ‘ወንድ ልጅ ተፀነሰ’ የተባለበት ሌሊት።
4ያ ቀን ጨለማ ይሁን፥
እግዚአብሔር ከላይ አይፈልገው፥
ብርሃንም አይብራበት።
5ጨለማና የሞት ጥላ የራሳቸው ገንዘብ ያድርጉት፥
ዳመናም ይረፍበት፥
የቀን ጨለማ ያሸብረው።
6ያን ሌሊት ጨለማ ይያዘው፥
በዓመቱ ቀኖች መካከል ደስ አይበለው፤
በወሮች ውስጥ ገብቶ አይቈጠር።
7እነሆ፥ ያ ሌሊት መካን ይሁን፥
እልልታ አይግባበት።
8ሌዋታንን ለማንቀሳቀስ የተዘጋጁ
ቀኑን የሚረግሙ ይርገሙት።
9የንጋቱ ኮከቦች ይጨልሙ፤
ብርሃንን ቢጠባበቅ አያግኘው፥
የንጋትንም ቅንድብ አይይ፥
10የእናቴን ማኅፀን ደጅ አልዘጋምና፥
መከራንም ከዓይኔ አልሰወረምና።
11በማኅፀን ሳለሁ ስለምን አልሞትሁም?
ከሆድስ በወጣሁ ጊዜ ስለምን ፈጥኜ አልጠፋሁም?
12ጉልበቶች ስለምን ተቀበሉኝ?
ጡትስ ስለምን ጠባሁ?
13አሁን ተኝቼ ዝም ባልሁ ነበር፥
አንቀላፍቼ ባረፍሁ ነበር፤
14የፈረሰውን ለራሳቸው ከሚሠሩት
ከምድር ነገሥታትና አማካሪዎች ጋር፥
15ወይም ወርቅ ከነበራቸው ገዢዎች፥
ቤታቸውንም በብር ከሞሉ ጋር፥
16ወይም እንደ ተደበቀበ ጭንጋፍ፥
ብርሃንም እንዳላዩ ሕፃናት በሆንሁ ነበር።
17ክፉዎች በዚያ መናደዳቸውን ይተዋሉ፥
በዚያም ደካሞች ያርፋሉ።
18በዚያ ግዞተኞች በአንድነት ተዘልለው ተቀምጠዋል፥
የአስጨናቂውን ድምፅ አይሰሙም።
19ታናሽና ታላቅ በዚያ አሉ፥
አገልጋይም ከጌታው ነጻ ወጥቶአል።
20በመከራ ላሉት ብርሃን፥
ነፍሳቸው መራራ ለሆነችባቸው፥
21 # ራእ. 9፥6። የተሰወረ ሀብትን ከሚቈፍሩ ይልቅ
ሞትን ለሚጠብቁ ለማያገኙትም፥
22መቃብርን ባገኙ ጊዜ
በእልልታ ደስ ለሚላቸው፥ ሐሤትንም ለሚያደርጉ
ሕይወት ስለምን ተሰጠ?
23መንገዱ ለተሰወረበት ሰው፥
እግዚአብሔርም በአጥር ላጠረው
ብርሃን ስለምን ተሰጠ?
24ከእንጀራዬ በፊት ልቅሶዬ መጥቶአልና፥
ጩኸቴም እንደ ውኃ ፈስሶአል።
25የፈራሁት ነገር መጥቶብኛልና፥
የደነገጥሁበትም ደርሶብኛል።
26ተዘልዬ አልተቀመጥሁም፥ አልተማመንሁም፥ አላረፍሁም፥
ነገር ግን መከራ መጣብኝ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ