መጽሐፈ ኢዮብ 2
2
1ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የእግዚአብሔር ልጆች#2፥1 መላእክት። በጌታ ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣን ደግሞ በጌታ ፊት ለመቆም በመካከላቸው መጣ። 2ጌታም ሰይጣንን፦ “ከወዴት መጣህ?” አለው። ሰይጣንም፦ “በምድር ላይ ዞርሁ፥ በእርሷም ተመላለስሁ” ብሎ ለጌታ መለሰ። 3ጌታም ሰይጣንን፦ “በውኑ አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም፥ ያለ ምክንያት ይጠፋ ዘንድ በእርሱ ላይ ብትገፋፋኝም እንኳን፥ እስከ አሁን ፍጹምነቱን ጠብቋል።” 4ሰይጣንም መልሶ ጌታን እንዲህ አለው፦ “በቆዳ ላይ ቆዳ#2፥4 ፈሊጣዊ አነጋገር ይመስላል፤ ኢዮብ ገና በብርቱ አልተፈተነም፥ ወደ ውስጥ የሚዘልቅ መከራ ይድረስበት ለማለት ነው።፥ ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል። 5ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ አጥንቱንና ሥጋውን ዳስስ፥ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።” 6ጌታም ሰይጣንን፦ “ሕይወቱን ተወው እንጂ እነሆ፥ እርሱ በእጅህ ነው” አለው።
7ሰይጣንም ከጌታ ፊት ወጣ፥ ኢዮብንም ከእግሩ መርገጫ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቁስል መታው። 8ኢዮብም ሥጋውን ይፍቅበት ዘንድ ገል ወሰደ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ። 9ሚስቱም፦ “እስከ አሁን ፍጹምነትህን ይዘሃልን? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት” አለችው። 10እርሱ ግን፦ “አንቺ ከሰነፎች#2፥10 ሥራ የማይወዱ ማለት ሳይሆን እግዚአብሔርን የማያከብሩ ማለት ነው። ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፥ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን?” አላት። በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም።
11ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች ይህን የደረሰበትን ክፉ ነገር ሁሉ ሰምተው ከየአገራቸው መጡ፥ እነርሱም ቴማናዊው ኤልፋዝ፥ ሹሐዊው ቢልዳድ፥ ነዕማታዊው ሶፋር ነበሩ። እነርሱም ሊያዝኑለትና ሊያጽናኑት በአንድነት ወደ እርሱ ለመምጣት ተስማሙ። 12ከሩቅም ሆነው ዓይናቸውን ባነሡ ጊዜ አላወቁትም፤ ድምፃቸውንም አሰምተው አለቀሱ፥ እያንዳንዳቸውም መጐናጸፊያቸውን ቀደዱ፥ ወደ ላይም ወደ ራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ። 13ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊትም ከእርሱ ጋር በምድር ላይ ተቀመጡ፥ ሕመሙም እጅግ እንደ በዛ አይተው ነበርና ከእነርሱ አንድ ቃል የሚናገረው አልነበረም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 2: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ