መጽሐፈ ኢዮብ 24

24
1“ሁሉን የሚችል አምላክ የወሰናቸውን ጊዜያት#24፥1 እግዚአብሔር የሚፈርድበት ጊዜ። ለምን አያሳውቅም?
የሚያውቁትስ ቀኖቹን ለምን አያዩም?
2የድንበሩን ምልክት የሚያፈርሱ አሉ፥
መንጋዎቹን ቀምተው ያሰማራሉ።
3የወላጅ አልባውን አህያ ይነዳሉ፥
የመበለቲቱን በሬ ለመያዣነት ይወስዳሉ።
4ድሆቹን ከመንገድ ያስወጣሉ፥
የምድርም ችግረኞች ሁሉ ይሸሸጋሉ።
5እነሆ፥ በምድረ በዳ እንዳሉ እንደ ሜዳ አህዮች፥
መብልን ፈልገው ወደ ሥራቸው ይወጣሉ፥
ምድረ በዳውም ለልጆቻቸው መብልን ይሰጣቸዋል።
6እነዚያ በእርሻ ውስጥ እህላቸውን ያጭዳሉ፥
የበደለኛውንም ወይን ይቃርማሉ።
7ራቁታቸውን ያለ ልብስ ያድራሉ፥
በብርድ ጊዜ የሚደረብ የላቸውም።
8ከተራሮች በሚወርድ ዝናብ ይረጥባሉ፥
መጠጊያም አጥተው ቋጥኙን ያቅፋሉ።
9አባቱ የሞተበትን ልጅ ከጡቱ የሚነጥሉ አሉ፥
ከችግረኛውም መያዣ ይወስዳሉ።
10ያለ ልብስ ራቁታቸውን ይሄዳሉ፥
ተርበው ነዶዎችን ይሸከማሉ#24፥10 ለአሠሪዎቻቸው የሚጠቅም ነዶ።
11በእነዚህ ሰዎች አጥር ውስጥ ዘይት ያወጣሉ፥
ወይንም ይጠምቃሉ፥ ነገር ግን ይጠማሉ።
12በከተማው ለመሞት የሚያጣጥሩ ያቃስታሉ፥
ቁስለኞችም ለእርዳታ ይጮኻሉ፥
እግዚአብሔር ግን ልመናቸውን አይመለከትም።”
13“እነዚህ በብርሃን ላይ የሚያምፁ ናቸው፥
መንገዱን አያውቁም፥ በጎዳናውም አይጸኑም።
14ነፍሰ ገዳዩም ሳይነጋ ማልዶ ይነሣል፥
ችግረኞችንና ድሆችን ይገድላል፥
በሌሊትም እንደ ሌባ ነው።
15የአመንዝራ ሰው ዐይን ጨለማን#24፥15 ደንገዝገዝ ሲል። ይጠብቃል፦
የማንም ዐይን አያየኝም ይላል፥
ፊቱንም ይሸፍናል።
16ቤቶቹን በጨለማ ይሰረስራሉ፥
በቀን ይሸሸጋሉ፥
ብርሃንም አያውቁም።
17የጥዋት ብርሃን ለእነርሱ ሁሉ እንደ ሞት ጥላ ነው፥
የሞትን ጥላ አስደንጋጭነት ያውቃሉና።”
18“እነርሱ በውኃ ላይ ተንሳፈው ያልፋሉ፥
ድርሻቸውም በምድር ላይ የተረገመች ናት፥
ወደ ወይኑ ቦታ መንገድ አይመለሱም።
19ድርቅና ሙቀት የበረዶውን ውኃ ያጠፋሉ፥
እንዲሁ ሲኦል በደለኞችን ታጠፋለች።
20ማኅፀን ትረሳዋለች፥
ትልም በደስታ ይጠባዋል፥
ዳግመኛም የሚያስታውሰው የለም፥
ክፋትም እንደ ዛፍ ይሰበራል።”
21“የማትወልደውን መካኒቱን ይበድላታል፥
ለመበለቲቱም መልካም አያደርግም።
22ነገር ግን በኃይሉ ኃያላንን ያስቀጥላል፥
እርሱም በተነሣ ጊዜ ሰው በሕይወቱ አይታመንም።
23እግዚአብሔር በደኅና አኑሮአቸዋል፥
በዚያም ይታመናሉ፥
ዐይኖቹ ግን መንገዳቸውን ይመለከታሉ።
24ጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፥
ይሄዳሉ፥ ይጠወልጋሉም፥
እንደ ሌሎች ሁሉ ይከማቻሉ፥
እንደ እሸትም ራስ ይቈረጣሉ።
25እንዲህስ ባይሆን ሐሰተኛ የሚያደርገኝ፥
ነገሬንስ እንደ ከንቱ የሚያደርገው ማን ነው?”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ