መጽሐፈ ኢዮብ 21

21
1ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦
2“ስሙ፥ ቃሌን ስሙ፥
ይህም እንደ ማጽናናት ይቆጠርላችሁ።
3እናገር ዘንድ ተውኝ፥
ከተናገርሁም በኋላ ተሳለቁ።
4በውኑ የኀዘን እንጉርጉሮዬን ለሰው እናገራለሁን?
አለመታገሤ ተገቢ አይደለምን?
5ወደ እኔ ተመልከቱ፥ ተደነቁም፥
እጃችሁንም በአፋችሁ ላይ አኑሩ።
6እኔ ባሰብሁ ቍጥር እደነግጣለሁ፥
ሰውነቴንም መንቀጥቀጥ ይይዘዋል።
7ስለምን ክፉዎች በሕይወት ይኖራሉ?
ስለ ምንስ ያረጃሉ? ኃይላቸውንስ ስለምን ያጠነክራሉ?
8ዘራቸው ከእነርሱ ጋር ጸንቶ ይኖራል፥
ልጆቻቸውም በዓይናቸው ፊት ናቸው።
9ቤታቸው በሰላም ከፍርሃት ነጻ ነው፥
የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም።
10ኮርማቸው ይወልዳል፥ ዘሩንም አይጥለውም፥
ላማቸውም ትወልዳለች፥ አትጨነግፍም።
11ሕፃኖቻቸውን እንደ መንጋ ይለቃሉ፥
ልጆቻቸውም ይቧርቃሉ።
12ከበሮና መሰንቆ ወስደው ይዘምራሉ፥
በእምቢልታ ድምፅ ደስ ይላቸዋል።
13ዕድሜያቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ፥
በሰላምም ወደ ሲኦል ይወርዳሉ።”
14እግዚአብሔርንም፦ “ከእኛ ዘንድ ራቅ፥
መንገድህን እናውቅ ዘንድ አንወድድም።
15እናመልከውስ ዘንድ ሁሉን የሚችል አምላክ ማን ነው?
ወይስ ወደ እርሱ ብንጸልይ ምን ይጠቅመናል?” ይላሉ።
16“እነሆ፥ ሀብታቸው በእጃቸው ውስጥ አይደለምን?
የክፉዎች ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት።”
17“የክፉዎች መብራት የጠፋው፥
መቅሠፍትም የመጣባቸው፥
እግዚአብሔርም በቁጣው መከራ የከፈላቸው፥
18በነፋስ ፊት እንደ ገለባ፥
ዐውሎ ነፋስም እንደሚወስደው ትቢያ የሆኑት ስንት ጊዜ ነው?”
19እናንተ፦ “እግዚአብሔር በደላቸውን ለልጆቻቸው ይጠብቃል” ብላችኋል።
ይልቁንም እራሳቸው ይረዱት ዘንድ ፍዳን ይክፈላቸው።
20ዐይኖቻቸው ጥፋታቸውን ይዩ፥
ሁሉን ከሚችል አምላክ ቁጣ ይጠጡ።
21የወራታቸውስ ቍጥር ከተቈረጠ፥
ከእነርሱ በኋላ የቤታቸው ደስታ ምን ይሆናቸዋል?
22ከፍ ከፍ ባሉት ላይ ለሚፈርደው እግዚአብሔር
ሰው እውቀትን ሊያስተም ይችላልን?
23አንድ ሰው በሰላም ተረጋግቶ ሲቀመጥ
ከነሙሉ ኃይሉ ሳለ ይሞታል።
24በአንጀቱ ውስጥ ስብ ሞልቶአል፥
የአጥንቶቹም ቅልጥም ረጥቦአል።
25ሌላውም ሰው መልካምን ነገር ከቶ ሳይቀምስ
በተመረረች ነፍስ ይሞታል።
26በአፈር ውስጥ በአንድ ላይ ይተኛሉ፥
ትልም ይከድናቸዋል።
27“እነሆ፥ ሐሳባችሁን፥
የመከራችሁብኝንም ክፉ ምክር አውቄዋለሁ።
28እናንተ፦ የከበርቴው ቤት የት ነው?
ክፉዎች ያደሩበት ድንኳን የት ነው? ብላችኋል።
29መንገደኞችን አልጠየቃችሁምን?
ምስክርነታቸውንስ አትረዱምን?
30ክፉ ሰው በመቅሠፍት ቀን እንደሚተርፍ፥
በቁጣው ቀን እንደሚድን።
31ስለ መንገዱ ፊቱ ለፊት የሚወቅሰው ማን ነው?
ስለ ሠራውስ የሚቀጣው ማን ነው?
32እርሱን ግን ለቀብር ይሸከሙታል፥
መቃብሩም ይጠበቃል።
33የሸለቆው ጓል ይጣፍጥለታል፥
በኋላውም ሰው ሁሉ ይከተለዋል፥
በፊቱም ቍጥር የሌለው ጉባኤ አለ።
34የምትመልሱልኝ ውስልትና ነውና
በከንቱ እንዴት ታጽናኑኛላችሁ?”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ