የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ወንጌል 1:1-51

የዮሐንስ ወንጌል 1:1-51 መቅካእኤ

በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱ በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ አንድም ነገር ያለ እርሱ የሆነ የለም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፤ ሕይወትም የሰዎች ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፤ ጨለማም አላሸነፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክርነት መጣ፤ ሁሉም በእርሱ በኩል ያምኑ ዘንድ። ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፤ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፤ ዓለም ግን አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፤ ነገር ግን የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑበትን ሥልጣን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በእኛም ዘንድ አደረ፤ ጸጋንና እውነትን የተመላውን፥ የአባቱ አንድያ ልጅ በአባቱ ዘንድ ያለውን ክብሩንም አየን። ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ፤ እንዲህም ብሎ ጮኸ “‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤’ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ።” እኛ ሁላችንም ከሙላቱ ተቀበልን፥ በጸጋ ላይ ጸጋን፤ ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። እግዚአብሔርን ያየው ከቶ ማንም የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ገለጠው። አይሁድም “አንተ ማን ነህ?” ብለው ለመጠየቅ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። መሰከረም፤ አልካደምም፤ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤” ብሎ መሰከረ። “እንግዲያውስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?” ብለው ጠየቁት። “አይደለሁም” አለ። “ነቢዩ ነህን?” “አይደለሁም” ብሎ መለሰ። “እንግዲያውስ ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፥ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። እርሱም “ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ ‘የጌታን መንገድ አቅኑ’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ነኝ” አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩ፤ “እንግዲያውስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፥ ስለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት። ዮሐንስ መልሶ “እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ነው፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የተገበሁ አይደለሁም” አላቸው። ይህ የሆነው ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ ነበር። በማግሥቱ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። ‘አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይበልጣል፤’ ብዬ ስለ እርሱ የተናገርሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን እርሱ ለእስራኤል እንዲገለጥ ነው በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁት።” ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ “መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሲወርድና በእርሱ ላይም ሲኖር አየሁ። እኔም አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን በውሃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ ‘መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው፤’ አለኝ። እኔም አይቻለሁ፥ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክሬአለሁ።” በማግሥቱ ዮሐንስ ከሁለት ደቀመዛሙርቱ ጋር እንደገና እዚያ ቆሞ ነበር፤ ኢየሱስንም ሲራመድ ተመልክቶ “እነሆ የእግዚአብሔር በግ፤” አለ። ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት። ኢየሱስም መለስ ብሎ ሲከተሉትም አይቶ “ምን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ረቢ!፥ (ሲተረጎም ‘መምህር ሆይ’ ማለት ነው) የምትኖረው የት ነው?” አሉት፤ እርሱም “መጥታችሁ እዩ፤” አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፤ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ ጊዜው ወደ ዐሥር ሰዓት ገደማ ነበር። ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ። እርሱ አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና “መሢሕን አግኝተናል” አለው፤ ትርጓሜውም “ክርስቶስ” ማለት ነው። ወደ ኢየሱስም አመጣው። ኢየሱስም ተመልክቶ “አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ ትባላለህ” አለው፤ ትርጓሜውም “ጴጥሮስ” ማለት ነው። በማግሥቱ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊሄድ ፈለገ፤ ፊልጶስንም አገኘውና “ተከተለኝ” አለው። ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ። ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ “ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል፤” አለው። ናትናኤልም “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን?” አለው። ፊልጶስ “መጥተህ እይ” አለው። ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ “ተንኰል የሌለበት እውነተኛ የእስራኤል ሰው እነሆ!” አለ። ናትናኤልም “እንዴት አወቅኸኝ?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ ዛፍ ሥር ሆነህ፥ አየሁህ፤” አለው። ናትናኤልም መልሶ “መምህር ሆይ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለው። ኢየሱስም መልሶ “ከበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ፤” ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” አለው።

Free Reading Plans and Devotionals related to የዮሐንስ ወንጌል 1:1-51