የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ወንጌል 1:1-51

የዮሐንስ ወንጌል 1:1-51 አማ05

ቃል በመጀመሪያ ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ይህም ቃል እግዚአብሔር ነበረ። እርሱ በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጠረ፤ ከተፈጠረው ሁሉ፥ አንድም ነገር ያለ እርሱ የተፈጠረ የለም። በእርሱ ሕይወት ነበረ፤ ይህም ሕይወት የሰዎች ብርሃን ነበረ። ብርሃን በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም ብርሃንን አያሸንፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ በእርሱ ምስክርነት ሰው ሁሉ እንዲያምን ስለ ብርሃን ምስክር ሆኖ መጣ። እርሱ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። እርሱም በዓለም ነበረ፤ ዓለምም የተፈጠረው በእርሱ ነው፤ ዓለም ግን አላወቀውም። ወደ ወገኖቹ መጣ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። ይሁን እንጂ ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን መብት ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሰው ዘር፥ ማለትም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከሰው ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በመካከላችን ኖረ፤ የአባቱ አንድያ ልጅ በአባቱ ዘንድ እንዳለው ያለውን ክብሩን አይተናል። ዮሐንስም “ ‘ያ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለነበረ ከእኔ እጅግ ይበልጣል’ ብዬ የነገርኳችሁ እነሆ፥ ይህ ነው” እያለ መሰከረ። ከእርሱ የጸጋ ሙላት እኛ ሁላችን በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀብለናል። ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጠ፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። እግዚአብሔርን ያየው ከቶ ማንም የለም፤ ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ያለው አንድያ ልጁ ብቻ ገለጠው። የአይሁድ ባለሥልጣኖች ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን ወደ ዮሐንስ ልከው፦ “አንተ ማን ነህ?” ብለው ባስጠየቁት ጊዜ የሰጠው ምስክርነት የሚከተለው ነው፤ እርሱ “እኔ መሲሕ አይደለሁም” ሲል መሰከረ እንጂ አልካደም። እነርሱም “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “አይደለሁም” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም “ይመጣል የተባለው ነቢይ ነህን?” አሉት። እርሱም “አይደለሁም” አለ። እነርሱም “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ለላኩን ሰዎች መልሱን እንድንነግር ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። እርሱም “ነቢዩ ኢሳይያስ እንደ ተናገረው እኔ ‘የጌታን መንገድ አቅኑ’ እያለ በበረሓ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ነኝ” አለ። ሰዎቹ የተላኩት ከፈሪሳውያን ነበረ፤ ስለዚህ “አንተ መሲሕ ወይም ኤልያስ ወይም ይመጣል የተባለው ነቢይ ካልሆንክ ታዲያ፥ ስለምን ታጠምቃለህ?” ሲሉ ጠየቁት። ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ የማጠምቀው በውሃ ነው፤ ነገር ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል። እርሱ ከእኔ በኋላ የሚመጣ ነው፤ እኔ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የበቃሁ አይደለሁም።” ይህ የሆነው ዮሐንስ ያጠምቅ በነበረበት ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ በምትገኘው በቢታንያ ከተማ ነው። በማግስቱ ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ይህ ነው! ‘ያ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ እጅግ ይበልጣል’ ያልኳችሁ ይህ ነው። እኔም ራሴ አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ እንዲገለጥ እኔ በውሃ እያጠመቅሁ መጣሁ።” ቀጥሎም ዮሐንስ እንዲህ ሲል መሰከረ፦ “መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ ከሰማይ ሲወርድና በእርሱ ላይ ሲያርፍበት አየሁ፤ እኔ ራሴ አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝ፥ ‘መንፈስ ቅዱስ ሲወርድና በእርሱ ላይ ሲያርፍበት የምታየው በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው’ ሲል ነግሮኛል። እኔም ይህን አይቼአለሁ፤ ስለዚህ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እመሰክራለሁ።” በማግስቱ ዮሐንስ ከሁለት ደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደገና እዚያ ቆሞ ነበር፤ ዮሐንስ ኢየሱስን በዚያ ሲያልፍ አይቶ፥ “እነሆ፥ የእግዚአብሔር በግ!” አለ። ሁለቱ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ዮሐንስ ይህን ሲል ሰምተው፥ ኢየሱስን ተከተሉት። ኢየሱስ መለስ ብሎ ሲከተሉት አየና “ምን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ረቢ! የምትኖረው የት ነው?” አሉት። (ረቢ ማለት መምህር ማለት ነው) እርሱም “ኑና እዩ” አላቸው። ስለዚህ ሄዱና የት እንደሚኖር አዩ። በዚያን ቀን ከእርሱ ጋር አብረው ዋሉ፤ ጊዜው ወደ ዐሥር ሰዓት ገደማ ነበር። ዮሐንስ የተናገረውን ቃል ሰምተው ኢየሱስን ከተከተሉት ደቀ መዛሙርት አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበር። እንድርያስ በመጀመሪያ ወደ ወንድሙ ወደ ስምዖን ሄደና “መሲሕን አገኘነው!” አለው። (መሲሕ ማለት ክርስቶስ ማለት ነው።) ከዚህ በኋላ እንድርያስ ስምዖንን ወደ ኢየሱስ አመጣው። ኢየሱስም ትኲር ብሎ ተመለከተውና “አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ኬፋ ትባላለህ” አለው። (ኬፋ ማለት ጴጥሮስ ወይም አለት ማለት ነው።) በማግስቱ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ለመሄድ ፈለገ፤ ፊልጶስንም አገኘውና “ተከተለኝ!” አለው። ፊልጶስ እንደ እንድርያስና እንደ ጴጥሮስ የቤተ ሳይዳ ከተማ ሰው ነበረ። ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፥ “ሙሴ በሕግ መጽሐፍ፥ ነቢያትም በትንቢት መጻሕፍት ስለ እርሱ የጻፉለትን አገኘነው፤ እርሱም የዮሴፍ ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው” አለው። ናትናኤል ግን፥ “ከናዝሬት መልካም ነገር ከቶ ሊገኝ ይችላልን?” አለው። ፊልጶስም “መጥተህ እይ!” አለው። ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ኢየሱስ “እነሆ! ተንኰል የሌለበት እውነተኛ የእስራኤል ሰው!” ሲል ስለ እርሱ ተናገረ። ናትናኤልም “የት ታውቀኛለህ?” አለው። ኢየሱስም “ፊልጶስ ሳይጠራህ በፊት ከበለስ ዛፍ ሥር ሆነህ አይቼሃለሁ” ሲል መለሰለት። በዚህ ጊዜ ናትናኤል፥ “መምህር ሆይ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ! አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ!” አለ። ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “አንተ ያመንከው፥ ‘ከበለስ ዛፍ ሥር ሆነህ አይቼሃለሁ’ ስላልኩህ ነውን? ከዚህ የበለጡ ነገሮችን ገና ታያለህ። እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፦ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔር መላእክትም በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ።”

Free Reading Plans and Devotionals related to የዮሐንስ ወንጌል 1:1-51