ትንቢተ ኤርምያስ 9

9
1ተወግተው ስለ ሞቱት ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ሰዎች ሌሊትና ቀን እንዳለቅስ ራሴ ውኃ፥ ዓይኔም የእንባ ምንጭ በሆነልኝ!
በፍጹም ከእዚህ ሕዝብ ጋር መኖር አለመቻሉ
2ሁሉም አመንዝሮች፥ የአታላዮች ጉባኤ ናቸውና ሕዝቤን እንድተው፥ ከእነርሱም ተለይቼ እንድሄድ በምድረ በዳ የመንገደኞች ማደሪያን ማን በሰጠኝ? 3ምላሳቸውን ስለ ሐሰት እንደ ቀስት ገተሩ፤ በምድር በረቱ ነገር ግን ለእውነት አይደለም፤ ከክፋት ወደ ክፋት ይሄዳሉና፥ እኔንም አላወቁምና፥ ይላል ጌታ። 4ወንድምም ሁሉ ያሰናክላልና፥ ባልንጀራም ሁሉ ያማልና እናንተ ሁሉ ከባልንጀሮቻችሁ ተጠንቀቁ፥ በወንድሞቻችሁም አትታመኑ። 5ሰውም ሁሉ ባልንጀራውን ያታልላል በእውነትም አይናገሩም፤ ሐሰትን መናገርንም ምላሳቸው ተምሮአል፥ ክፉንም ለማድረግ ይደክማሉ። 6ማደሪያህ በሽንገላ መካከል ነው፥ ከሽንገላም የተነሣ እኔን ለማወቅ እንቢ ብለዋል፥ ይላል ጌታ።
7ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ አቀልጣቸዋለሁ እፈትናቸዋለሁም፤ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ክፋት ከዚህ ሌላ የማደርገው ምንድነው? 8ምላሳቸው የተሳለ ፍላጻ ነው፤ ሽንገላን ይናገራሉ፤ ሰው ከባልንጀራው ጋር በሰላም ይናገራል፥ በልቡ ግን ያደባበታል። 9በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀስፋቸውምን? ይላል ጌታ፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን?
በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የልቅሶ እንጉርጉሮ
10“ለተራሮች ልቅሶንና እንጉርጉሮን ለምድረ በዳ ማሰማርያዎችም ዋይታን አነሣለሁ፥ ሰው እንዳያልፍባቸው ባድማ ሆነዋልና። ሰዎችም የከብቱን ድምፅ አይሰሙም፤ ከሰማይ ወፎች ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ሸሽተው ሄደዋል። 11ኢየሩሳሌምንም የፍርስራሽ ክምር የቀበሮም ማደሪያ አደርጋታለሁ፥ የይሁዳንም ከተሞች ሰው የማይቀመጥባት ባድማ አደርጋቸዋለሁ።”
12ይህን የሚያስተውል ጠቢብ ሰው ማን ነው? እንዲያውጅስ የጌታ አፍ ለማን ተናገረ? ሰው እንዳያልፍባት ምድርስ ስለምን ጠፋች፥ እንደ ምድረ በዳስ ስለምን ተቃጠለች? 13ጌታም እንዲህ አለ፦ “የሰጠኋቸውን ሕጌን ትተዋልና፥ ድምፄንም አልሰሙምና፥ በእርሱም አልተመላለሱምና፥ 14ነገር ግን የልባቸውን እልከኝነትና አባቶቻቸው ያስተማሩአቸውን በኣሊምን ተከትለዋልና 15ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይህን ሕዝብ እሬትን አበላዋለሁ የሐሞትንም ውኃ አጠጣዋለሁ። 16እነርሱና አባቶቻቸውም ባላወቁአቸው አሕዛብ መካከል እበትናቸዋለሁ፥ እስካጠፋቸውም ድረስ በስተ ኋላቸው ሰይፍን እልክባቸዋለሁ።”
የኢየሩሳሌም ሕዝብ ለልቅሶ እንዲዘጋጅ ጌታ መናገሩ
17የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “አስተውሉ፥ እንዲመጡም አልቃሾች ሴቶችን ጥሩ፤ እንዲመጡም ወደ ብልሃተኞች ሴቶች ላኩ፤ 18ዐይኖቻችንም እንባ እንዲያፈስሱ የዓይናችንም ሽፋሽፍቶች ውኃን እንዲያፈልቁ ፈጥነው ለእኛ ልቅሶውን ያነሳሱ። 19በጽዮን፦ ‘እንዴት ተበዘበዝን! ምድሪቱንም ትተናልና፥ ቤቶቻችንንም አፍርሰዋልና እንዴት አብዝተን አፈርን!’ የሚል የልቅሶ ድምፅ ተሰምቶአል።” 20እናንተ ሴቶች ሆይ! የጌታን ቃል ስሙ፥ ጆሮአችሁም የአፉን ቃል ትቀበል፥ ለሴቶች ልጆቻችሁም ልቅሶውን፥ እያንዳንዳችሁም ለባልንጀሮቻችሁ ዋይታውን አስተምሩ። 21ሕፃናቱን ከመንገድ ጉልማሶቹንም ከአደባባይ ለማጥፋት ሞት ወደ መስኮታችን ደርሶአል ወደ ንጉሥ ቅጥሮቻችን ውስጥ ገብቶአል። 22ተናገር፥ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘የሰውም ሬሳ እንደ ጉድፍ በእርሻ ላይ፥ ማንምም እንደማይሰበስበው ከአጫጆች በኋላ እንደሚቀር ቃርሚያ ይወድቃል።’ ”
23ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ 24#1ቆሮ. 1፥31፤ 2ቆሮ. 10፥17።ነገር ግን የሚመካው፦ ጽኑ ፍቅርንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ ጌታ መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ ነገሮች እነዚህ ናቸውና፥ ይላል ጌታ።”
25“እነሆ፥ ሸለፈታቸውን ብቻ የተገረዙትን ሁሉ የምቀጣበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ፥ 26እንዲሁም የእስራኤል ቤት ሁሉ ልባቸው ያልተገረዘ ነውና፥ አሕዛብም ሁሉ ያልተገረዙ ናቸውና ግብጽንና ይሁዳን፥ ኤዶምያስንም፥ የአሞንንም ልጆች፥ ሞአብንም፥ በምድረ በዳም የተቀመጡትን ጠጉራቸውን በዙሪያ የተላጩትን ሁሉ በዚያን ዘመን እቀጣለሁ።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ