ትንቢተ ኤርምያስ 51

51
1ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በባቢሎን ላይና በሌብ-ቃምያ#51፥1 በዕብራይስጥ ለከለደዳውያን የተሰጠ ኅቡእ ስም ነው። በሚኖሩት ላይ አጥፊውን ነፋስ አስነሣለሁ። 2በባቢሎንም ላይ የሚያዘሩትን ሰዎች እልካለሁ እነርሱም ያዘሩአታል፥ ምድርዋንም ባዶ ያደርጋሉ፤ በመከራም ቀን በዙሪያዋ ይከብቡአታል። 3ቀስተኛው ቀስቱን አይገትር ጥሩሩንም ለብሶ አይነሣ፤ ለጐልማሶችዋ አትዘኑ ሠራዊትዋንም ሁሉ አጥፉ። 4በከለዳውያንም ምድር ተገድለው፥ በሜዳዋም ላይ ተወግተው ይወድቃሉ።
5ምድራቸው በእስራኤል ቅዱስ ላይ በተሠራው በደል ምንም እንኳ የተሞላች ብትሆን፥ እስራኤልም ሆነ ይሁዳ በአምላካቸው በሠራዊት ጌታ ዘንድ አልተተዉም። 6ከባቢሎን ውስጥ ሽሹ፥ እያንዳንዳችሁም ነፍሳችሁን አድኑ፤ በበደልዋ አትጥፉ፥ የጌታ የበቀል ጊዜ በእርሷ ላይ ነውና፥ እርሱም ብድራትዋን ይከፍላታልና። 7#ራእ. 17፥2-4፤ 18፥3።ባቢሎን በጌታ እጅ ውስጥ ምድርን ሁሉ ያሰከረች የወርቅ ጽዋ ነበረች፥ አሕዛብም ከወይን ጠጅዋ ጠጥተዋል፤ ስለዚህ አሕዛብ እንደ እብድ ሆነዋል። 8ባቢሎን በድንገት ወደቀች ተሰበረችም፤ አልቅሱላት፥ ምናልባት ትፈወስ እንደሆነ ለቁስልዋ የሚቀባውን መድኃኒት ውሰዱላት። 9#ራእ. 18፥5።ባቢሎንን ልንፈውሳት ሞከርን፥ እርሷ ግን አልተፈወሰችም፤ ፍርድዋ እስከ ሰማይ ደርሶአልና፥ እስከ ደመናም ድረስ ከፍ ከፍ ብሏልና ትታችኋት እያንዳንዳችን ወደ አገራችን እንሂድ። 10ጌታ ጽድቃችንን በግልጥ አውጥቶአል፤ ኑ፥ በጽዮን የአምላካችንን የጌታን ሥራ እንናገር።
11ፍላጾችን ሳሉ ጋሻዎችንም አንሡ፤ ጌታ ሊያጠፋት አሳቡ በባቢሎን ላይ ነውና የሜዶንን ነገሥታት መንፈስ አስነሥቶአል፤ የጌታ በቀል ስለ መቅደሱ ሲል የሚበቀለው በቀል በእርሷ ላይ ነውና። 12በባቢሎን ቅጥሮች ላይ ዓላማውን አንሡ፥ ጥበቃን አጠናክሩ፥ የጥበቃን ሰዎች አቁሙ፥ ድብቅ ጦር አዘጋጁ፤ በባቢሎን በሚኖሩት ላይ የተናገረውን ጌታ አስቦታልና እንዲሁም ደግሞ አድርጎታልና። 13#ራእ. 17፥1።አንቺ በብዙ ውኃ አጠገብ የተቀመጥሽ፥ በመዝገቦችም የበለጠግሽ ሆይ! የእንጀራሽ ገመድ ተበጥሶዋል ፍጻሜሽ ደርሶአል። 14የሠራዊት ጌታ እንዲህ ሲል በራሱ ምሎአል፦ በእውነት ብዛታቸው እንደ አንበጣ በሚሆኑ ሰዎች እሞላሻለሁ፥ እነርሱም የአሸናፊነትን ጩኸት የይጮኹብሻል።
15ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለምን በጥበቡ የመሠረተ፥ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው። 16ድምጹን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይታወካሉ፥ ከምድርም ዳር ደመናትን ከፍ ያደርጋል፤ ለዝናብም መብረቅን ያደርጋል፥ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል። 17ሰው ሁሉ ቂላ ቂልና እውቀት የሌለው ሆኖአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፤ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስትንፋስም የላቸውምና። 18እነርሱ ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው፤ በተጐበኙ ጊዜ ይጠፋሉ። 19የያዕቆብ ድርሻ እንደ እነዚህ አይደለም፥ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነውና፥ ስሙ የሠራዊት ጌታ ነው።
እስራኤል የፈጣሪ መገልገያ መሣርያ መሆንዋ
20አንቺ መዶሻዬና የጦር መሣሪያዬ ነሽ፤ በአንቺ አሕዛብን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም መንግሥታትን አጠፋለሁ፤ 21በአንቺ ፈረሱንና ፈረሰኛውን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ሠረገላውንና በላዩ የሚቀመጠውን እሰባብራለሁ፤ 22በአንቺም ወንድንና ሴትን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ሽማግሌውንና ብላቴናውን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ጐልማሳውንና ድንግሊቱን እሰባብራለሁ፤ 23በአንቺም እረኛውንና መንጋውን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም አራሹንና ጥማጁን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ገዢዎችንና ሹማምቶችን አሰባብራለሁ።
የባቢሎን መጠጥፋት
24በጽዮን በዓይናችሁ ፊት ስለ ሠሩት ክፋታቸው ሁሉ በባቢሎንና በከለዳውያን ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ፍዳቸውን እከፍላለሁ፥ ይላል ጌታ።
25አንተ ምድርን ሁሉ የምታጠፋ አጥፊው ተራራ ሆይ! እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ፤ እጄንም እዘረጋብሃለሁ፥ ከዓለትም ራስ ላይ አንከባልልሃለሁ፥ የተቃጠለም ተራራ አደርግሃለሁ። 26ከአንተም ለማዕዘንና ለመሠረት የሚሆን ድንጋይ አይወስዱም፥ ለዘለዓለምም ባድማ ትሆናለህ፥ ይላል ጌታ።
27በምድር ላይ ዓላማን አንሡ በአሕዛብም መካከል መለከት ንፉ፥ አሕዛብንም ለጦርነት በእርሷ ላይ አዘጋጁ፤ የአራራትንና የሚኒን የአስከናዝንም መንግሥታት ጥሩባት አለቃንም በእርሷ ላይ ሹሙ፤ እንደ ጠጉራም ኩብኩባ ፈረሶችን በእርሷ ላይ አውጡ። 28አሕዛብን የሚዶንንም ነገሥታት ገዢዎችዋንም ሹማምንቶችዋንም ሁሉ የግዛትዋንም ምድር ሁሉ በእርሷ ላይ ለጦርነት አዘጋጁ። 29ማንም እንዳይቀመጥባት የባቢሎንን ምድር ባድማ ለማድረግ የጌታ አሳብ በባቢሎን ላይ ጸንቶአልና ምድር ተናወጠች ተወራጨችም። 30የባቢሎን ኃያላን መዋጋትን ትተዋል በምሽጎቻቸውም ውስጥ ተቀምጠዋል፤ ኃይላቸውም ደክሙአል እንደ ሴቶችም ሆነዋል፤ ማደሪያዎችዋም ነድደዋል መቀርቀሪያዎችዋም ተሰብረዋል። 31ከዳር እስከ ዳር ድረስ ከተማው እንደ ተያዘች ለባቢሎን ንጉሥ ለመንገር አንደኛው ሯጭ ሌላውን ሯጭ አንዱም መልእክተኛ ሌላውን መልእክተኛ ለመገናኘት ይሮጣል። 32የወንዙም መሻገርያዎች ተይዘዋል፥ የውኃ ማቆርያዎቹም በእሳት ተቃጥለዋል ወታደሮቹም በሽብር ውስጥ ናቸው።
33የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ “የባቢሎን ሴት ልጅ በመረገጥ ላይ እንዳለ ዐውድማ ነች፤ ጥቂት ቈይታ የመከር ጊዜ ይደርስባታል።” 34የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በላኝ፥ አደቀቀኝም፥ እንደ ባዶ ዕቃም አደረገኝ፥ እንደ ዘንዶም ዋጠኝ፥ ከሚጣፍጠውም ምግቤ ሆዱን ሞላ፥ እኔንም አውጥቶ ተፋኝ። 35በጽዮን የሚኖሩ እንዲህ ይበሉ፦ “በእኔና በሥጋ ዘመዶቼ ላይ የተደረገ ግፍ በባቢሎን ላይ ይሁን” ኢየሩሳሌምም እንዲህ ትበል፦ “ደሜ በከለዳውያን ምድር በሚኖሩት ላይ ይሁን”። 36ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሙግትሽን እምዋገትልሻለሁ በቀልሽንም እበቀልልሻለሁ፤ ባሕርዋንም አደርቀዋለሁ ምንጭዋንም እንዲደርቅ አደርጋለሁ። 37ባቢሎንም የፍርስራሽ ክምር፥ የቀበሮ ማደሪያ ሰውም የማይቀመጥባት መሣቀቅያና ማፍዋጫ ትሆናለች። 38በአንድነትም እንደ አንበሶች ያገሣሉ፥ እንደ አንበሳም ደቦሎች ያጉረመርማሉ። 39ሞቅ ባላቸው ጊዜ ደስ እንዲላቸው ለዘለዓለምም አንቀላፍተው እንዳይነቁ የመጠጥ ግብዣ አደርግላቸዋለሁ አሰክራቸዋለሁም፥ ይላል ጌታ። 40እንደ ጠቦቶችና እንደ አውራ በጎች እንደ አውራ ፍየሎችም ወደ መታረድ አወርዳቸዋለሁ።
41ሼሻክ#51፥41 በዕብራይስጥ ለባቢሎናውያን የተሰጠ ኅቡእ ስም ነው። እንዴት ተያዘች! ምድርም ሁሉ የሚያመሰግናት እንዴት ተወሰደች! ባቢሎንም በአሕዛብ መካከል መሣቀቅያ እንዴት ሆነች! 42ባሕሩ በባቢሎን ላይ ወጥቶባታል በሚናወጠውም ሞገዱ ተሸፍናለች። 43ከተሞችዋ ባድማና ደረቅ ምድር ምድረ በዳም፥ ሰውም የማይቀመጥባቸው የሰውም ልጅ የማያልፍባቸው ምድር ሆኑ። 44በባቢሎንም ውስጥ ቤልን እቀጣለሁ የዋጠውንም ከአፉ አስተፋዋለሁ፤ አሕዛብም ከዚያ ወዲያ ወደ እርሱ አይነጉዱም፥ የባቢሎንም ቅጥር ወድቆአል።
45ሕዝቤ ሆይ! ከመካከልዋ ውጡ እያንዳንዱም ሰው ከጌታ ጽኑ ቁጣ ነፍሱን ያድን። 46በምድሪቱም ከሚሰማው ወሬ የተነሣ ልባችሁ የዛለ አይሁን አትፍሩም፤ በአንዱም ዓመት አንድ ወሬ፥ በሚቀጥለውም ዓመት ሌላ ወሬ ይመጣል፥ በምድሪቱም ላይ ዓመጽ ይሆናል፥ ገዢም በገዢ ላይ ይነሣል። 47ስለዚህ፥ እነሆ፥ የተቀረጹትን የባቢሎን ምስሎች የምቀጣበት ዘመን ይመጣል፥ ምድርዋም ሁሉ ያፈረች ትሆናለች ተወግተውም የሞቱት ሁሉ በመካከልዋ ይወድቃሉ። 48#ራእ. 18፥20።አጥፊዎች ከሰሜን ይመጡባታልና ሰማይና ምድር በእነርሱም ያለው ሁሉ በባቢሎን ላይ እልል ይላሉ፥ ይላል ጌታ። 49#ራእ. 18፥24።ለባቢሎን በምድሪቱ ሁሉ ተወግተው የሞቱት ወድቀዋል እንዲሁ ለእስራኤል ተወግተው ለሞቱት ባቢሎን መውደቅ አለባት።
50ከሰይፍ ያመለጣችሁ ሆይ! ሂዱ፥ አትቁሙ፤ በሩቅ ስፍራ ሆናችሁ ጌታን አስታውሱ፥ ኢየሩሳሌምንም በልባችሁ አስቡአት። 51ስድብን ስለ ሰማን አፍረናል፤ ባዕዳን ሰዎችም በጌታ ቤት ውስጥ ወዳሉት ወደ ተቀደሱ ስፍራዎች ገብተዋልና ውርደት ፊታችንን ሸፍኖታል። 52ስለዚህ፥ እነሆ፥ የተቀረጹትን ምስሎችዋን የምቀጣበት በምድርዋም ላይ ሁሉ የተወጋው የሚያቃስትበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ። 53ምንም እንኳ ባቢሎን ወደ ሰማይ ብትወጣ፥ የኃይልዋንም ከፍታ ብታጠናክር፥ ከእኔ ዘንድ አጥፊዎች ይመጡባታል፥ ይላል ጌታ።
54ከባቢሎን ጩኸት፥ ከከለዳውያንም ምድር የታላቅ ጥፋት ድምፅ ተሰምቶአል። 55ጌታ ባቢሎንን አጥፍቶአታልና፥ ከእርሷም ታላቁን ድምፅ ዝም አሰኝቶአልና፤ ሞገዳቸውም እንደ ብዙ ውኆች ይተምማል፥ የድምፃቸውም ጩኸት ያስገመግማል። 56አጥፊው በባቢሎን ላይ መጥቶባታልና፥ ኃያላኖችዋ ተያዙ፥ ቀስታቸውም ተሰባበረ፤ ጌታ ፍዳን የሚከፍል አምላክ ነውና፥ ፍዳንም በእርግጥ ይከፍላል። 57አለቆችዋንና ጥበበኞችዋንም፥ ገዢዎችዋንና ሹማምቶችዋን ኃያላኖችዋንም አሰክራለሁ፥ ለዘለዓለምም አንቀላፍተው አይነቁም፥ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ የተባለው ንጉሥ። 58“የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሰፋፊዎቹ የባቢሎን ቅጥሮች ፈጽመው ይፈርሳሉ ረጃጅሞችም በሮችዋ በእሳት ይቃጠላሉ፤ ሕዝቡም በከንቱ ጉልበቱን ይፈስሳል፥ አሕዛብም የደከሙበት ነገር ለእሳት ይሆናል።”
ለሠራያ የተሰጠ የነቢዩ የኤርምያስ ትእዛዝ
59የመሕሤያ ልጅ የኔርያ ልጅ ሠራያ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ከእርሱ ጋር ወደ ባቢሎን በሄደ ጊዜ ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘው ቃል ይህ ነው። ሠራያም የሻለቃ መጋቢ ባሻ አዛዥ ነበረ። 60በባቢሎንም ላይ የሚመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ፥ ስለ ባቢሎን የተጻፈውን ይህን ቃል ሁሉ፥ ኤርምያስ በመጽሐፍ ላይ ጻፈው። 61ኤርምያስም ሠራያን እንዲህ አለው፦ “ወደ ባቢሎን በገባህ ጊዜ ልብ ብለህ ይህን ቃል ሁሉ አንብብና፥ 62እንዲህ በል፦ ‘አቤቱ፥ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ማንም እንዳይቀመጥባት፥ ለዘለዓለምም ባድማ እንድትሆን ልታጠፋት በዚህች ስፍራ ላይ አንተ ተናግረሃል።’ 63#ራእ. 18፥21።ይህንም መጽሐፍ ማንበብ ከፈጸምህ በኋላ፥ ድንጋይን እሰርበት በኤፍራጥስም ወንዝ መካከል ጣለው፤ 64አንተም እንዲህ በል፦ ‘እኔ ከማመጣባት ክፉ ነገር የተነሣ እንዲሁ ባቢሎን ትሰጥማለች አትነሣምም።’ ”#51፥64 ዕብራይስጡ “እነርሱም ይደክማሉ” ይጨምራል። የኤርምያስ ቃላት እስከዚህ ድረስ ነው።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ