ትንቢተ ኤርምያስ 52
52
የኢየሩሳሌም መጥፋት ዳግመኛ መታየቱ
1ሴዴቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አንድ ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ የእናቱም ስም አሚጣል ይባል ነበር፥ እርሷም የሊብና ሰው የሆነው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 2ኢዮአቄምም እንዳደረገው ሁሉ በጌታ ፊት ክፉ የሆነውን ነገር አደረገ። 3በእርግጥ ከጌታ ቁጣ የተነሣ ከፊቱ አውጥቶ እስኪጥላቸው ድረስ ይህ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሆነ፤ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።
4 #
ሕዝ. 24፥2። ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ መጥተው ከበቡአት በዙሪያዋም ለመክበብያ የሚሆን ምሽግ ሠሩባት። 5ከተማይቱም እስከ ንጉሡ ሴዴቅያስ ዐሥራ አንደኛው ዓመት ድረስ ተከብባ ነበር። 6በአራተኛውም ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማይቱ ራብ ጸንቶ ነበር፥ ለአገሬውም ሰው እንጀራ ታጣ። 7#ሕዝ. 33፥21።የከተማይቱም ቅጥር ተጣሰ፥ ወታደሮችም ሁሉ ሸሹ፥ በሁለቱም ቅጥሮች መካከል ባለው በር ወደ ንጉሡ አትክልት በሚወስደው መንገድ በሌሊት ከከተማይቱ ወጡ። ከለዳውያንም በከተማይቱ ዙሪያ ነበሩ፤ ወደ ዓረባም በሚወስደው መንገድ ሄዱ። 8የከለዳውያንም ሠራዊት ንጉሡን ተከታተሉት፥ በኢያሪኮም ሜዳ ሴዴቅያስን ደረሱበት፤ ሠራዊቱም ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ተበትነው ነበር። 9ንጉሡንም ያዙት፥ እርሱንም የባቢሎን ንጉሥ ወዳለባት በሐማት ምድር ወዳለችው ወደ ሪብላ አመጡት፤ እርሱም ፍርድን በእርሱ ላይ ተናገረ። 10የባቢሎንም ንጉሥ የሴዴቅያስን ልጆች ዓይኑ እያየ ገደላቸው፥ እንዲሁም የይሁዳን አለቆች ሁሉ በሪብላ ገደላቸው። 11#ሕዝ. 12፥13።የሴዴቅያስንም ዐይኖች አወጣ፤ የባቢሎንም ንጉሥ በሰንሰለት አሰረው ወደ ባቢሎንም ወሰደው፥ እስኪሞትም ድረስ በእስር ቤት አኖረው።
12በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር በዓሥራ ዘጠነኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን በባቢሎን ንጉሥ ፊት የሚያገለግለው የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። 13#1ነገ. 9፥8።የጌታን ቤትና የንጉሡን ቤት አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምንም ቤቶች ሁሉ፥ ታላላቆችን ቤቶች ሁሉ፥ በእሳት አቃጠለ። 14ከዘበኞቹም አለቃ ጋር የነበረው የከለዳውያን ሠራዊት ሁሉ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ያለውን ቅጥር ሁሉ አፈረሰ። 15የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን የሕዝቡን ድኆች፥ በከተማይቱም ውስጥ የተረፈውን ሕዝብ፥ ሸሽተውም ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን፥ የተረፉትንም የእጅ ሞያተኞች አፈለሰ። 16የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ከአገሩ ድኆች ወይን ተካዮችና አራሾች እንዲሆኑ አስቀረ።
17 #
1ነገ. 7፥15-47። ከለዳውያንም በጌታ ቤት የነበሩትን የናስ ዓምዶች በጌታም ቤት የነበሩትን የውኃ ማመላለሻ ፉርጎዎችንና የናሱን ኩሬ ሰባበሩ፥ ናሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰዱ። 18የሸክላ ድስቶችንና መጫሪያዎችንም፥ መኰስተሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችንም፥ ሙዳዮችና#52፥18 የዕጣን ማስቀመጫ። የሚገለገሉባቸውንም የናስ ዕቃዎች ሁሉ ወሰዱ። 19የዘበኞቹም አለቃ ወጭቶቹንና ማንደጃዎቹን፥ ጐድጓዳ ሳሕኖቹንና የሸክላ ድስቶቹን፥ መቅረዞችንና ሙዳዮችን መንቀሎችንም፥ የወርቁን ዕቃ በወርቅ፥ የብሩንም ዕቃ በብር አድርጎ፥ ወሰደ። 20ንጉሡ ሰሎሞንም ለጌታ ቤት ያሠራቸውን ሁለቱን ዓምዶች፥ አንዱንም ኩሬ፥ ከኩሬውና ከውኃ ማመላለሻ ፉርጎዎቹም በታች የነበሩትን ዐሥራ ሁለቱን የናስ በሬዎች ወሰደ፤ ለእነዚህ ከናስ ለተሠረሩ ዕቃዎች ሁሉ መመዘኛ ሚዛን አልነበረም። 21እነዚህም ዓምዶች፥ የአንዱ ዓምድ ቁመት ዐሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፥ የዙሪያውም ልኬት ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ ውፍረቱም አራት የጣት ስንዝር ያህል ነበረ፥ መሀል ለመሀልም ክፍት ነበረ። 22የናሱም ጉልላት በላዩ ነበረ፤ የአንዱም ጉልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበረ፥ በጉልላቱም ላይ በዙሪያው ሁሉ ከናስ የተሠሩ መረበብና ሮማኖች ነበሩበት፤ በሁለተኛውም ዓምድ ደግሞ እንደዚህ ያለ ነገርና ሮማኖች ነበሩበት። 23በስተ ውጭም በኩል ዘጠና ስድስት ሮማኖች ነበሩ። በመረበቡም ዙሪያ የነበሩ ሮማኖች ሁሉ አንድ መቶ ነበሩ።
24የዘበኞቹም አለቃ ታላቁን ካህን ሠራያን በማዕረጉም ሁለተኛ የነበረውን ካህን ሶፎንያስን የደጃፉም ጠባቂዎች የነበሩትን ሦስቱን ሰዎች ወሰደ፤ 25ከከተማይቱም በወታደሮች ላይ ተሾሞ ከነበረው አንዱን አዛዥ፥ በከተማይቱም ውስጥ ከተገኙት የንጉሡ አማካሪዎች ሰባቱን ሰዎች፥ የአገሩንም ሕዝብ ለጦርነት የሚመለምለውን የሠራዊቱን አለቃ ጸሐፊ፥ በከተማይቱም ከተገኙት ከአገሩ ሕዝብ ስልሳ ሰዎች ወሰደ። 26የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ወስዶ የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጣቸው። 27የባቢሎንም ንጉሥ መታቸው፥ በሐማትም ምድር ባለችው በሪብላ ገደላቸው። እንዲሁ ይሁዳ ከአገሩ ተማረከ።
28ናቡከደነፆር ማርኮ ያፈለሰው የሕዝብ ቍጥር ብዛት ይህ ነው፤ በሰባተኛው ዓመት ሦስት ሺህ ሀያ ሦስት አይሁድ፤ 29በናቡከደነፆርም በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት ስምንት መቶ ሠላሳ ሁለት ሰው ከኢየሩሳሌም ማርኮ አፈለሰ፤ 30በናቡከደነፆር በሀያ ሦስተኛው ዓመት የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ከአይሁድ ሰባት መቶ አርባ አምስት ሰው ማርኮ አፈለሰ፤ በአጠቃላይ የሰዎቹ ብዛት አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበር።
31እንዲህም ሆነ፤ የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት በዓሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያ አምስተኛው ቀን፥ የባቢሎን ንጉሥ ኤዌል ማሮዴክ በነገሠ በአንደኛው ዓመት ለይሁዳ ንጉሥ ለዮአኪን ቸርነት አደረገለት ከእስር ቤትም አወጣው፤ 32በመልካምም ተናገረው፥ ዙፋኑንም ከእርሱ ጋር በባቢሎን ከነበሩት ነገሥታት ዙፋን በላይ አደረገለት። 33ዮአኪንም በእስር ቤትም ውስጥ ለብሶት የነበረውን ልብስ ለወጠ፥ በሕይወቱም ዘመን ሁሉ በንጉሡ ገበታ ሁልጊዜ እንጀራ ይበላ ነበር። 34ስለ እርሱም ቀለብ የባቢሎን ንጉሥ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ፥ እስኪሞት ድረስ፥ በየዕለቱ የሚያስፍልገውን የዘወትር ቀለብ ይሰጠው ነበር።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 52: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ