ትንቢተ ኤርምያስ 32
32
በወረራው ጊዜ ነቢዩ ኤርምያስ የገዛው እርሻ
1 #
2ነገ. 25፥1-7። በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በአሥረኛው ዓመት፥ በናቡከደነፆር በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት፥ ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2በዚያን ጊዜም የባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከብቦ ነበር፤ ነቢዩም ኤርምያስ በይሁዳ ንጉሥ ቤት በነበረው በእስር ቤት አደባባይ ታስሮ ነበር። 3የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ እንዲህ ብሎ አሳስሮት ነበርና፦ “ስለምን እንዲህ ብለህ ትንቢት ትናገራለህ፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ እርሱም ይይዛታል፤ 4የይሁዳም ንጉሥ ሴዴቅያስ በእውነት በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፎ ይሰጣል፥ ፊት ለፊትም ያነጋግረዋል፥ ዓይኑም ዓይኑን ያያል እንጂ ከከለዳውያን እጅ አያመልጥም፤ 5እርሱም ሴዴቅያስን ወደ ባቢሎን ያፈልሰዋል፥ እኔም እስክጐበኘው ድረስ በዚያ ይኖራል፥ ይላል ጌታ፤ ከከላዳውያን ጋር ብትዋጉ ምንም አይቀናችሁም’?”
6ኤርምያስም እንዲህ አለ፦ “የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 7እነሆ፥ የአጐትህ የሰሎም ልጅ አናምኤል ወደ አንተ መጥቶ፦ ‘በመግዛት የመቤዠት መብት የአንተ ነውና በዓናቶት ያለውን እርሻዬን ግዛ’ ይልሃል። 8እንደ ጌታም ቃል የአጐቴ ልጅ አናምኤል እኔ ወዳለሁበት ወደ ግዞቱ ቤት አደባባይ መጥቶ፦ ‘በብንያም አገር በዓናቶት ያለውን እርሻዬን፥ እባክህ፥ ግዛ፤ የርስቱና የመቤዠቱ መብት የአንተ ነውና፤ ለአንተ ግዛው’ አለኝ። ይህም የጌታ ቃል እንደሆነ አወቅሁ። 9በዓናቶትም ያለውን እርሻ ከአጐቴ ልጅ ከአናምኤል ገዛሁ፥ ዐሥራ ሰባት ሰቅል ብርም መዘንሁለት። 10በውሉም ሰነድ ላይ ፈረምሁ አተምሁትም፥ ምስክሮችንም ጠርቼ ብሩን በሚዛን መዘንሁለት። 11የተገዛበትን የውሉን ዝርዝር ሁኔታና ደንብ የያዘውን የታተመውን የውል ሰነድ እንዲሁም ካልታተመው#32፥11 ግልጽ ከሆነው ግልባጭ ጋር ወሰድሁ፤ 12የአጐቴም ልጅ አናምኤል፥ የተገዛበትን የውሉን ሰነድ የፈረሙት ምስክሮች፥ በእስርም ቤት አደባባይ የተቀመጡት አይሁድ ሁሉ እያዩ የተገዛበትን የውሉን ሰነድ ለመሕሤያ ልጅ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት። 13በፊታቸውም እንዲህ ብዬ ባሮክን አዘዝሁት፦ 14‘የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ብዙ ቀን ተጠብቀው እንዲቆዩ የታተመውን ይህን የተገዛበትን የውል ሰነድና ካልታተመው የውል ሰነድ ጋር በአንድ ላይ ወስደህ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኑራቸው። 15የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ሰዎች በዚህች ምድር ቤትንና እርሻን የወይን ቦታንም እንደገና ይገዛሉ።’”
ስለ ማሰተዋል ነቢዩ ኤርምያስ መጸለዩ
16“ለኔርያ ልጅ ለባሮክም የተገዛበትን የውሉን ሰነድ ከሰጠሁት በኋላ፥ እንዲህ ብዬ ወደ ጌታ ጸለይሁ፦ 17‘አቤቱ ጌታ ሆይ! ወዮ! እነሆ፥ በእውነት አንተ ሰማይንና ምድርን በታላቅ ኃይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፥ ለአንተም ከቶ የሚሳንህ ምንም ነገር የለም። 18ለብዙ ሺህ ትውልድ ጽኑ ፍቅርን ታሳያለህ፥ የአባቶችንም በደል ከእነርሱ በኋላ በልጆቻቸው ብብት ትመልሳለህ፤ ታላቅና ኃያል አምላክ ሆይ! ስምህ የሠራዊት ጌታ ነው። 19በምክር ታላቅ በሥራም ብርቱ ነህ፤ ለሁሉም እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ፍሬ ለመስጠት ዐይኖችህ በአዳም ልጆች መንገድ ሁሉ ተገልጠዋል። 20ምልክትንና ድንቅን ነገር በግብጽ ምድር፥ እስከ ዛሬም ድረስ በእስራኤልና በሌሎች ሰዎች መካከል አድርገሃል፥ በዚህም እስከ ዛሬዋ ቀን ስምህን አጽንተሃል። 21በምልክትና በድንቅ ነገር፥ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ በታላቅም ግርማ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብጽ ምድር አወጣህ። 22ለአባቶቻቸው ለመስጠት የማልህላቸውን፥ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ይህችን ምድር፥ ሰጠሃቸው፤ 23እነርሱም ገብተው ወረሱአት፤ ነገር ግን ድምፅህን አልሰሙም በሕግህም አልሄዱም፥ እንዲያደርጉም ካዘዝሃቸው ሁሉ ምንም አላደረጉም፤ ስለዚህ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣህባቸው። 24እነሆ፥ አፈር ደልድለው የመሸጉ፥ ከተማይቱን ሊይዙአት ቀርበዋል፤ ከሰይፍና ከራብ ከቸነፈርም የተነሣ ከተማይቱ ለሚዋጉአት ለከለዳውያን እጅ ተሰጥታለች፤ የተናገርኸውም ሆኖአል፥ እነሆም፥ አንተ ታየዋለህ። 25ምንም እንኳ ከተማይቱ ለከለዳውያን እጅ ተላልፋ ብትሰጥም፤ አቤቱ ጌታ ሆይ! አንተ ግን፦ “እርሻውን በብር ግዛ ምስክሮችንም ጥራ” አልኸኝ።’ ”
ጌታ ሕዝቡ እንደሚመለስ ማረጋገጫ መስጠቱ
26የጌታም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 27እነሆ፥ እኔ የሥጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ የሆንሁ ጌታ ነኝ፤ በውኑ ለእኔ የሚሳነኝ ነገር አለን? 28#2ነገ. 25፥1-11፤ 2ዜ.መ. 36፥17-21።ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይህችን ከተማ ለከለዳውያን እጅና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እርሱም ይይዛታል። 29ይህችን ከተማ የሚወጉ ከለዳውያን መጥተው በእሳት ያነድዱአታል፥ እኔንም ለማስቈጣት በሰገነታቸው ላይ ለበዓል ካጠኑባቸው፥ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥን ቁርባን ካፈሰሱባቸው ቤቶች ጋር ያቃጥሉአታል። 30የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች ከታናሽነታቸው ጀምሮ በፊቴ ክፉ ነገርን ብቻ አድርገዋልና፤ የእስራኤልም ልጆች እኔን በእጃቸው ሥራ ከማስቈጣት በቀር ሌላ ሥራ አላደረጉምና፥ ይላል ጌታ። 31ይህች ከተማ ከሠሩአት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ቁጣዬንና መዓቴን አነሣሥታለችና ከፊቴ አስወግዳታለሁ፤ 32ይህንንም የማደርገው እኔን ለማስቈጣት፥ እነርሱና ነገሥታቶቻቸው፥ አለቆቻቸውና ካህናቶቻቸው፥ ነብዮቻቸውና የይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ፥ ስላደረጉት ስለ እስራኤል ልጆችና ስለ ይሁዳ ልጆች ክፋት ሁሉ ነው። 33ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ወደ እኔ መለሱ፤ እኔም በማለዳ ተነሥቼ ባለማቋረጥ ባስተምራቸውም እንኳ ተግሣጽን ለመቀበል አልሰሙም። 34#2ነገ. 23፥10፤ ኤር. 7፥30፤31፤ 19፥1-6።ሊያረክሱትም ስሜ በተጠራበት ቤት ውስጥ ርኩሰታቸውን አኖሩ። 35#2ነገ. 23፥10፤ ኤር. 7፥31፤ ዘሌ. 18፥21።ይሁዳን ኃጢአት ለማሠራት፥ ይህን ርኩሰት እንዲያደርጉ ባላዛቸውም በልቤም ባላስበውም፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለሞሌክ በእሳት ለመሠዋት፥ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ያሉትን የበዓልን የኮረብታውን መስገጃዎች ሠሩ።
36“ስለዚህ አሁን ግን የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ አንተ ስለ እርሷ፦ ‘በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ተሰጥታለች’ ስለምትላት ከተማ እንዲህ ይላል፦ 37እነሆ፥ በቁጣዬና በመዓቴ በታላቅም መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁባት አገር ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፥ በደኅንነትም እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ 38እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። 39እኔን ለዘለዓለም በመፍራት ለእነርሱም ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም እንዲሆንላቸው አንድ ልብና አንድ መንገድ እሰጣቸዋለሁ። 40ለእነርሱም ከማደርገው በጎነት አልመለስም ስል፥ ከእነርሱ ጋር የዘለዓለምን ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ ከእኔም ዘንድ ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ። 41ለእነርሱም መልካምን በማድረግ ደስ ይለኛል፥ በእውነትም በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ። 42ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ይህን እጅግ ክፉ ነገር ሁሉ በዚህ ሕዝብ ላይ እንዳመጣሁ፥ እንዲሁ ለእነርሱ የተናገርሁትን በጎነት ሁሉ አመጣላቸዋለሁ። 43እናንተም፦ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ያለች ባድማ ናት፥ ለከለዳውያንም እጅ ተሰጥታለች በምትሉአት ምድር እርሻን ይገዛሉ። 44ምርኮኞቻቸውንም እመልሳለሁና በብንያም አገር፥ በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፥ በይሁዳም ከተሞች፥ በደጋውም ባሉ ከተሞች፥ በቈላውም ባሉ ከተሞች፥ በደቡብም ባሉ ከተሞች ሰዎች እርሻውን በብር ይገዛሉ፥ ምስክሮችንም ጠርተው በውሉ ሰነድ ላይ ፈርመው ያትሙታል፥ ይላል ጌታ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 32: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ