ስለ ነቢያት፤ ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል አጥንቶቼም ሁሉ ታውከዋል፤ ከጌታ የተነሣ፥ ከቅዱስ ቃላቱም የተነሣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ። ምድር በአመንዝሮች ተሞልታለችና፥ ከመርገምም የተነሣ ምድር አልቅሳለች፤ የምድረ በዳውም ማሰማርዎች ደርቀዋል፤ አካሄዳቸውም ክፉ ነው፥ ብርታታቸውም ቅን አይደለም። ነቢዩና ካህኑም ረክሰዋልና፥ ሌላው ቀርቶ በቤቴ ውስጥ እንኳ ክፋታቸውን አግኝቻለሁ፥ ይላል ጌታ። ስለዚህ መንገዳቸው በጨለማ እንዳለች እንደ ምታዳልጥ ስፍራ ትሆንባቸዋለች፥ እነርሱም ወደ እርሷ ይገፈተራሉ ተፍገምግመውም ይወድቁባታል፤ እኔም በምጐበኛቸው ዓመት ክፉ ነገርን አመጣባቸዋለሁና፥ ይላል ጌታ። በሰማርያ ነቢያት መካከል አጸያፊን ነገር አይቻለሁ፤ በበዓል ትንቢት ይናገሩ ነበር፥ ሕዝቤንም እስራኤልን ያስቱ ነበር። በኢየሩሳሌምም ነቢያት መካከል አስደንጋጭ ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ በሐሰትም ይሄዳሉ፤ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ፤ ሁላቸውም እንደ ሰዶም የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ። ስለዚህ ስለ ነብያት የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ ከኢየሩሳሌም ነቢያት ዘንድ ርኩሰት በምድር ሁሉ ላይ ወጥቶአልና፥ እሬትን አበላቸዋለሁ የሐሞትንም ውኃ አጠጣቸዋለሁ።” የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃላት አትስሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሩአችኋል፤ ከጌታ አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ። ለሚንቁኝ ሁልጊዜ፦ ጌታ፦ ሰላም ይሆንላችኋል ብሏል ይላሉ፤ በልቡም እልከኝነት ለሚሄድ ሁሉ፦ ክፉ ነገር አያገኛችሁም ይላሉ። ቃሉን ለማየትና ለመስማት በጌታ ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠ የሰማስ ማን ነው? እነሆ፥ የጌታ ዐውሎ ነፋስ! ቁጣው ወጥቶአል፥ ጥቅል ዐውሎ ነፍስ፤ እርሱም በክፉዎች ራስ ላይ ይወርዳል። የጌታ ቁጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም፤ በኋለኛው ዘመን ፈጽማችሁ ታስተውሉታላችሁ። እኔ ሳልልካቸው እነዚህ ነቢያት ሮጡ፤ እኔም ሳልነግራቸው ትንቢትን ተናገሩ። በምክሬ ግን ቢቆሙ ኖሮ፥ ለሕዝቤ ቃሎቼን ባሰሙ ነበር፥ ከክፉም መንገዳቸው ከሥራቸውም ክፋት በመለሱአቸው ነበር። እኔ የቅርብ አምላክ ነኝን? ይላል ጌታ፥ የሩቅስ አምላክ አይደለሁምን? ሰው በስውር ቦታ ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ይላል ጌታ። ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል ጌታ። “አለምሁ አለምሁ” እያሉ በስሜ ትንቢትን በሐሰት የሚናገሩትን የነቢያትን ነገር ሰምቻለሁ። ትንቢትን በሐሰት በሚናገሩ፥ የልባቸውንም ሽንገላ በሚናገሩ በነቢያት ልብ ይህ የሚሆነው እስከ መቼ ነው? አባቶቻቸው ስለ በዓል ስሜን እንደ ረሱ፥ እንዲሁ አንዱ ከሌላው ጋር በሚነጋገሩት ሕልሞቻቸው ሕዝቤ ስሜን ለማስረሳት ያስባሉ። የሚያልም ነቢይ ሕልምን ይናገር፤ ቃሌም ያለበት ቃሌን በእውነት ይናገር። ገለባ ከስንዴ ጋር ምን አለው? ይላል ጌታ። በውኑ ቃሌ እንደ እሳት፥ ድንጋዩንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለችምን? ይላል ጌታ። ስለዚህ፥ እነሆ፥ አንዱ ከሌላው ዘንድ ቃሎቼን በሚሰርቁ ነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ። እነሆ፥ ከምላሳቸው ትንቢትን አውጥተው፦ “እርሱ ይላል” በሚሉ ነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ። እነሆ፥ ሐሰትን ትንቢት በሚያልሙ በሚናገሩም፥ በሐሰታቸውና በድፍረታቸውም ሕዝቤን በሚያስቱ በነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ፤ እኔም አልላክኋቸውም አላዘዝኋቸውምም፥ ለእነዚህም ሕዝብ በማናቸውም ነገር አይጠቅሙአቸውም፥ ይላል ጌታ። “ይህ ሕዝብ ወይም ነቢይ ወይም ካህን፦ ‘የጌታ ሸክም ምንድነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ፥ አንተ፦ ‘ሸክሙ እናንተ ናችሁ፥ እጥላችኋለሁም፥ ይላል ጌታ’ ትላቸዋለህ። ነቢይና ካህን ሕዝቡም ‘የጌታ ሸክም’ ብሎ ቢናገር፥ ያን ሰውና ቤቱን እቀጣለሁ። እያንዳንዱም ለባልንጀራው፥ እያንዳንዱም ለወንድሙ እንዲህ ይበልስ፦ ‘ጌታ የመለሰው ምንድነው? ጌታስ ምን ነገር ተናገረ?’ ለሰው ሁሉ ቃሉ ሸክም ይሆንበታልና ‘የጌታ ሸክም’ ብላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ አትጥሩ፤ የሠራዊትን ጌታ የአምላካችንን የሕያው እግዚአብሔርን ቃላት ለውጣችኋልና። ለነቢዩ እንዲህ ትለዋለህ፦ ‘ጌታ ምን መለሰልህ?’ ‘ጌታስ የተናገረው ምንድነው?’ ነገር ግን፦ ‘የጌታ ሸክም’ ብትሉ፥ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔ፦ ‘የጌታ ሸክም’ አትበሉ ብዬ ልኬባችኋለሁና፥ እናንተም ይህን ቃል፦ ‘የጌታ ሸክም’ ብላችኋልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ ፈጽሜ እረሳችኋለሁ፥ እናንተንም ለእናንተና ለአባቶቻችሁም የሰጠኋትን ከተማ ከፊቴ እጥላለሁ። የዘለዓለምንም ስድብ፥ ከቶም ተረስቶ የማይጠፋውን የዘለዓለምን እፍረት አመጣባችኋለሁ።”
ትንቢተ ኤርምያስ 23 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኤርምያስ 23:9-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች