ትንቢተ ኤርምያስ 11
11
እስራኤልና ይሁዳ ቃል ኪዳን ማፍረሳቸው
1ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2“የዚህን ቃል ኪዳን ቃላት ስማ፥ ለይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ተናገር፥ 3እንደዚህም በላቸው፦ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ የዚህን ቃል ኪዳን ቃላት የማይሰማ ሰው ርጉም ይሁን፥ 4ይህንንም ከግብጽ አገር ከብረት ምድጃ ባወጣኋቸው ቀን ለአባቶቻችሁ ያዘዝኩት ቃላት ነው፤ አልሁም፦ ድምፄን ስሙ፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። 5ይህ ዛሬ እንደሆነ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ለአባቶቻችሁ እንድሰጣቸው የማልሁትን መሐላ እንዳጸና ነው።” እኔም፦ “አቤቱ! አሜን” ብዬ መለስሁለት።
6ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህን ቃላት ሁሉ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ተናገር፥ እንዲህም በል፦ የዚህን ቃል ኪዳን ቃላት ስሙ አድርጉትም። 7አባቶቻችሁን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በማለዳ በመነሳት ደጋግሜ እያስጠነቀቅሁ፦ ድምፄን ስሙ በማለት አስጠንቅቄአቸው ነበር። 8እነርሱ ሁሉ ግን በክፉ ልባቸው እልከኝነት ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፤ ስለዚህ ያዘዝኋቸውን እነርሱም ያላደረጉትን የዚህን ቃል ኪዳን ቃላት ሁሉ አመጣሁባቸው።”
9ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “በይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም በሚኖሩ መካከል አድማ ተገኝቶአል። 10ቃሌንም ለመስማት እንቢ ወዳሉ ወደ ቀድሞው አባቶቻቸው ኃጢአት ተመለሱ፥ ሊያገለግሉአቸውም እንግዶችን አማልክት ተከተሉ፤ የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት ከአባቶቻቸው ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አፈረሱ። 11ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሊያመልጡት የማይችሉትን ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁ፥ ወደ እኔም ይጮኻሉ፤ እኔም አልሰማቸውም። 12በይሁዳም ከተሞችና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሄደው ወደሚያጥኑላቸው አማልክት ይጮኻሉ፤ ነገር ግን በመከራቸው ጊዜ ከቶ አያድኑአቸውም። 13ይሁዳ ሆይ! አማልክትህ እንደ ከተሞችህ ቍጥር እንዲሁ ናቸው፤ እንደ ኢየሩሳሌምም መንገዶች ቍጥር ለአሳፋሪ ነገር መሠዊያዎችን ሠርታችኋል፥ እነርሱም ለበዓል የምታጥኑባቸው መሠዊያዎች ናቸው። 14አንተም ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ከመከራቸው የተነሣ ወደ እኔ በጮኹ ጊዜ አልሰማቸውምና ስለ እነርሱም ጩኸትና ልመና አታድርግ።
15“ክፋትን አብዝታ በመሥራትዋ ወዳጄ በቤቴ ውስጥ ምን አላት? የተቀደሰ ሥጋ ክፋትሽን ከአንቺ ያስወግዳልን? ከዚያም ደስተኛ ትሆኛለሽን?” 16ጌታ ስምሽን፦ “በመልካም ፍሬ የተዋበች የለመለመች የወይራ ዛፍ” ብሎ ጠራው፤ በጽኑ ዐውሎ ነፋስ ጩኸት እሳትን አነደደባት፥ ቅርንጫፎችዋም ተሰብረዋል። 17ለበዓልም በማጠናቸው አስቈጡኝ፥ ለራሳቸው ስለ ሠሩአት ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ ቤት ክፋት የተከለሽ የሠራዊት ጌታ ክፉን ነገር ተናግሮብሻል።
የነቢዩ ኤርምያስ ሕይወት በአደጋ ላይ መሆኑ
18ጌታም አስታወቀኝ እኔም አወቅሁ፤ ሥራቸውንም ገለጥህልኝ። 19እኔም ለመታረድ እንደሚነዳ እንደ የዋህ በግ ጠቦት ሆንሁ፤ እነርሱም፦ “ዛፉን ከነፍሬው እናጥፋ፥ ስሙም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይታወስ ከሕያዋን ምድር እናስወግደው” ብለው ምክርን እንዳሰቡብኝ አላወቅሁም ነበር። 20#ጥበ. 1፥6-9።ነገር ግን ኩላሊትንና ልብን የምትመረምር በቅንም የምትፈርድ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ! ሙግቴን ገልጬልሃለሁና በእነርሱ ላይ የሚሆነውን በቀልህን ልይ። 21ስለዚህም፦ “በእጃችን እንዳትሞት በጌታ ስም ትንቢት አትናገር” ብለው ነፍስህን ስለሚሹ ስለ ዓናቶት ሰዎች 22የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እቀጣቸዋለሁ፤ ጉልማሶቻቸው በሰይፍ ይሞታሉ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም በራብ ይሞታሉ፤ 23በምጐበኛቸውም ዓመት በዓናቶት ሰዎች ላይ ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁና ማንም ከእነርሱ የሚተርፍ የለም።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 11: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ