የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 12

12
ነቢዩ ኤርምያስ ጌታ ጋር መሟገቱ
1አቤቱ! ከአንተ ጋር በተምዋገትሁ ጊዜ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ነገር ግን ከአንተ ጋር ስለ ፍርድ ልናገር። የኃጢአተኞች መንገድ ስለምን ይቃናል? በደልንስ ለሚበድሉ ሁሉ ስለምን ደኅንነት ይሆናል? 2ተክለሃቸዋል፤ ሥርም ሰድደዋል፤ አድገዋል ፍሬም አፍርተዋል፤ በአፋቸው አንተ ቅርብ ነህ፥ ከልባቸው ግን ሩቅ ነህ። 3አቤቱ! አንተ ግን፥ አውቀኸኛል፤ አይተኸኛል፥ ልቤንም ወደ አንተ መሆኑን ፈትነሃል፤ እንደ ሚታረድ በግ ጐትተህ ለያቸው፥ ለመታረድም ቀን አዘጋጃቸው። 4ምድሪቱ የምታለቅሰው፥ የአገሩ እጽዋት ሁሉ የሚደርቀው እስከ መቼ ነው? የተቀመጡባት ሰዎች፦ “ፍጻሜያችንን አያይም” ብለዋልና ስለ ክፋታቸው እንስሶችና ወፎች ተጠራርገው ጠፍተዋል።
ጌታ ለነቢዩ ኤርምያስ መልስ መስጠቱ
5“ከእግረኞች ጋር በሮጥህ ጊዜ እነርሱ ቢያደክሙህ፥ ከፈረሶች ጋር መታገል እንዴት ትችላለህ? በሰላምም ምድር ተሰናክለህ ከወደቅህ፥ በዮርዳኖስ ዱር እንዴት ታደርጋለህ? 6ወንድሞችህና የአባትህ ቤት እነርሱ ጭምር አታልለውሃልና፥ በኋላህም ጮኸዋልና፤ በመልካምም ቢናገሩህም አትመናቸው።”
7“ቤቴን ትቼአለሁ ርስቴንም ጥያለሁ፥ ነፍሴም የምትወድዳትን በጠላቶችዋ እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ። 8ርስቴ በዱር እንዳለ አንበሳ ሆናብኛለች፤ ድምፅዋን በእኔ ላይ አንሥታለች፤ ስለዚህ ጠልቻታለሁ። 9ርስቴ እንደ ዝንጉርጉር አሞራ ሆነችብኝን? አሞሮችስ በዙሪያዋና በላይዋ ሆነዋልን? ሂዱ፥ የምድር አራዊትን ሁሉ ሰብስቡ፥ እንዲበሉም አምጡአቸው። 10ብዙ እረኞች የወይኑን ቦታዬን አጥፍተዋል፥ እድል ፈንታዬንም ረግጠዋል፤ የአምሮቴን እድል ፈንታ ምድረ በዳ አድርገውታል። 11ባድማ አድርገውታል፥ ፈርሶም ወደ እኔ ያለቅሳል፤ ምድር ሁሉ ባድማ ሆናለች በልቡም የሚያስባት ማንም የለም። 12በምድረ በዳ ባሉ በተራቈቱ ኮረብቶች ሁሉ ላይ በዝባዦች መጥተዋል፥ የጌታ ሰይፍ ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይበላልና፤ ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም። 13ስንዴን ዘሩ እሾህንም አጨዱ፤ እራሳቸውን አደከሙ፥ ምንም አልረባቸውም፤ ስለ ጌታ ጽኑ ቁጣ በፍሬያችሁ ታፍራላችሁ።”
ጌታ ለእስራኤል ጎረቤቶች መናገሩ
14ጌታ ለሕዝቤ ለእስራኤል ያወረስሁትን ርስት ለሚነኩት ክፉዎች ጎረቤቶች ሁሉ እንዲህ ይላልና፦ “እነሆ፥ ከምድራቸው እነቅላቸዋለሁ፥ የይሁዳንም ቤት ከመካከላቸው እነቅለዋለሁ። 15ከነቀልኋቸውም በኋላ መልሼ እምራቸዋለሁ፥ እያንዳንዱንም ወደ ርስቱ እያንዳንዱንም ወደ ምድሩ እመልሳለሁ። 16በበዓል እንዲምል ሕዝቤን እንዳስተማሩ በስሜ፦ ‘በሕያው ጌታ እምላለሁ!’ ብለው እንዲምሉ የሕዝቤን መንገድ በትጋት ቢማሩ፥ በዚያን ጊዜ በሕዝቤ መካከል ይመሠረታሉ። 17ባይሰሙኝ ግን ያንን ሕዝብ ፈጽሜ እነቅለዋለሁ አጠፋዋለሁም፥ ይላል ጌታ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ