የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መሳፍንት 6

6
የጌዴዎን መጠራት
1እንደገና እስራኤላውያን በጌታ ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ ጌታም ለምድያማውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ሰባት ዓመት ገዟቸው። 2#1ሳሙ. 13፥6።እስራኤላውያን የምድያማውያን ኃይል ስለበረታባቸው በየዋሻውና በየምሽጉ፥ በየተራራው ጥግ መሸሸጊያ ስፍራ አበጁ። 3እስራኤላውያን ዘር በሚዘሩበት ጊዜ ሁሉ ምድያማውያን፥ አማሌቃውያንና ሌሎች የምሥራቅ ሕዝቦች መጥተው አገሩን ይወሩ ነበር። 4እነርሱም በምድሪቱ ላይ ሰፍረው እስከ ጋዛ ያለውን ሰብል በማጥፋት አንዳችም የእህልዘር አያስተርፉም፥ የበግም ሆነ የከብት ወይም የአህያ መንጋ አይተዉም ነበር። 5ከብቶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው ሲመጡ ልክ የአንበጣ መንጋ ይመስሉ ነበር፤ ሰዎቹንም ሆነ ግመሎቻቸውን ለመቁጠር አዳጋች ሲሆን፥ የሚመጡትም ምድሪቱን ለማጥፋት ነበር። 6#መሳ. 3፥9፤ 15፤ 4፥3፤ 10፥10፤ 1ሳሙ. 12፥8፤ 10።ምድያማውያን እስራኤላውያንን ችግር ላይ ስለጣሏቸው፥ ይረዳቸው ዘንድ ወደ ጌታ ጮኹ።
7ከምድያማውያን ጥቃት የተነሣ እስራኤላውያን ወደ ጌታ ጮኹ። 8#መሳ. 2፥1-3፤ 10፥11-14።ጌታ አንድ ነቢይ ላከላቸው፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል ከባርነት ቤት ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ነኝ። 9ከግብፃውያን እጅ ታደግኋችሁ፤ ከሚያስጨንቋችሁ ሁሉ አዳንኋችሁ፤ እነርሱንም ከፊታችሁ አሳድጄ አስወጣኋቸው፤ ምድራቸውንም ሰጠኋችሁ።” 10እናንተንም፥ “‘እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ፤ በምድራቸው ላይ የምትኖሩባቸው የአሞራውያንን አማልክት አታምልኩ’ አልኋችሁ፤ እናንተ ግን አላዳመጣችሁኝም።”
11 # ዕብ. 11፥32። የጌታ መልአክ ዖፍራ ወደምትባል መንደር መጥቶ፥ በአቢዔዝራዊው በኢዮአስ ዕርሻ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የባሉጥ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን፥ ምድያማውያን እንዳያዩት ተደብቆ በወይን መጭመቂያው ስፍራ ስንዴውን ይወቃ ነበር። 12የጌታ መልአክ ተገልጦለት “አንተ ኃያል ጦረኛ! እነሆ፥ ጌታ ከአንተ ጋር ነው” አለው። 13ጌዴዎን መልሶ፥ “ጌታዬ ሆይ ጌታ ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ እንዴት ሊደርስብን ቻለ? ‘ጌታ ከግብጽ ምድር አውጥቶናል’ በማለት አባቶቻችን የነገሩን ታምራት የት አለ? አሁን ግን ጌታ ትቶናል፤ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው። 14#ዘፀ. 3፥10-12።በዚህ ጊዜ ጌታ ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፥ “ባለህ ኃይል ሂድ፤ እስራኤውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ እንድታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን? አለው” 15#1ሳሙ. 9፥21።ጌዴዎንም፥ “ጌታ ሆይ የእኔ ጐሣ ከምናሴ ነገድ እጅግ ደካማ ነው፤ ከቤተሰቤም እኔ የመጨረሻ ነኝ፤ ታዲያ እንዴት እኔ እስራኤልን ላድን እችላለሁ?” አለ። 16ጌታም፥ “በእርግጥ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታቸዋለህ” አለው። 17ጌዴዎን እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “አሁን በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ በእርግጥ የምታነጋግረኝ አንተ ራስህ ለመሆንህ ምልክት ስጠኝ፤ 18ተመልሼ እስክመጣ፥ መሥዋዕቴንም አምጥቼ በፊትህ እስካቀርብ ድረስ እባክህ አትሂድ።” ጌታም፥ “እስክትመለስ እጠብቅሃለሁ” አለው። 19ጌዴዎን ወደ ቤቱ ሄደ፤ የፍየል ጠቦትም ዐረደ፤ አንድ ኢፍ መስፈሪያ ዱቄት ወስዶ እርሾ ያልገባበት ቂጣ ጋገረ። ሥጋውን በቅርጫት፥ መረቁን በምንቸት ይዞ በመምጣት በባሉጥ ሥር ለተቀመጠው አቀረበለት። 20#መሳ. 13፥19-22።የጌታ መልአክ፥ “ሥጋውን እርሾ ያልገባበትን ቂጣ ወስደህ፥ በዚያ ዐለት ላይ አኑር፤ መረቁንም በሥጋውና በቂጣው ላይ አፍስስ” አለው፤ ጌዴዎንም እንደ ታዘዘው አደረገ። 21መልአኩም በያዘው በትር ጫፍ ሥጋውንና ቂጣውን ነካ፤ ከዐለቱም እሳት ወጥቶ ሥጋውንና ቂጣውን በላ፤ ከዚያም የጌታ መልአክ ተሰወረ። 22#ዘፍ. 32፥31፤ ዘዳ. 5፥24-26፤ መሳ. 13፥22።ጌዴዎን ያየው የጌታ መልአክ መሆኑን ባወቀ ጊዜ፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ የጌታን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና ወዮልኝ” አለ። 23ጌታም፥ “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም” አለው። 24#ዘፍ. 33፥20፤ 35፥7፤ ዘፀ. 7፥15።ጌዴዎንም በዚያ ለጌታ መሠዊያ ሠራ፤ ስሙንም “ጌታ ሰላም ነው” ብሎ ጠራው፤ ይህ መሠዊያ የአቢዔዝራውያን ይዞታ በሆነው በዖፍራ ዛሬም ቆሞ ይታያል።
25በዚያች ሌሊት ጌታ ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ከአባትህ መንጋ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን ወይፈን ውሰድ፤ አባትህ ለበኣል የሠራውን መሠዊያ አፍርስ፤ በአጠገቡ የአሼራን ዐምድ ሰባብረህ ጣል። 26በዚህ ፍርስራሽ ጉብታ ላይ ለአምላክህ ለጌታ የሚገባውን መሠዊያ ሥራ። ሰባብረህ በጣልኸው የአሼራ ምስል ዐምድ ሁለተኛውን ወይፈን ወስደህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ አቅርበው።” 27ጌዴዎን ከአገልጋዮቹ ዐሥር ሰዎች ወስዶ ጌታ እንዳዘዘው አደረገ፤ ቤተሰቡንና የከተማውን ሰው ስለ ፈራ ይህን ያደረገው ቀን ሳይሆን ሌሊት ነበር።
28ሌሊቱ ነግቶ የከተማው ሕዝብ ከመኝታው ሲነሣ፥ የበኣል መሠዊያ ፈርሶ በአጠገቡ የቆመው የአሼራ ምስል ተሰባብሮ፥ አዲስ በተሠራው መሠዊያ ላይ ሁለተኛው ወይፈን ተሠውቶ ነበር። 29እነርሱም፥ “ይህን ያደረገ ማን ነው?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። ነገሩን በጥብቅ ሲከታተሉም፥ “የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን መሆኑን ደረሱበት።” 30የከተማይቱም ሰዎች ኢዮአስን፥ “የበኣልን መሠዊያ ያፈረሰና በአጠገቡ የቆመውን የአሼራን ምስል ዐምድ የሰበረው ልጅህ በመሆኑ መሞት ስላለበት አውጣልን አሉት።” 31#1ነገ. 18፥27።በዚህ ጊዜ ኢዮአስ በቊጣ ለገነፈለውና በዙሪያው ለነበረው ሕዝብ እንዲህ አለ፤ “ለበኣል ትሟገቱለታላችሁን? ልታድኑትስ ትሞክራላችሁን? ለእርሱ የሚሟገትለት ቢኖር እስከ ጠዋት ይሙት! እንግዲህ በኣል በእርግጥ አምላክ ከሆነ መሠዊያውን ሲያፈርሱበት ራሱን ሊከላከል ይችላል።” 32#1ሳሙ. 12፥11።ስለዚህም፥ “መሠዊያውን አፍርሶበታልና ራሱ በኣል ይሟገተው” ሲሉ በዚያ ዕለት ጌዴዎንን፥ “ይሩበኣል” ብለው ጠሩት።
33በዚህ ጊዜ ምድያማውያን ሁሉ፥ አማሌቃውያንና ሌሎች የምሥራቅ ሕዝቦች ያላቸውን አስተባብረው የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር በኢይዝራኤል ሸለቆ ሰፈሩ። 34#መሳ. 3፥10፤ 11፥29፤ 13፥25፤ 14፥6፤ 19፤ 15፥14፤ 1ሳሙ. 11፥6።ከዚያም የጌታ መንፈስ በጌዴዎን ላይ ወረደ፤ እርሱም መለከት ነፋ፤ አቢዔዝራውያን እንዲከተሉት ጠራቸው። 35እንዲሁም በመላው የምናሴ ምድር መልእክተኞቹን ልኮ እንዲከተሉት ጥሪ አደረገ፤ ደግሞም የአሴር፥ የዛብሎንና የንፍታሌም ሰዎች ወጥተው እንዲገጥሟቸው መልእክተኛ ላከባቸው።
36ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “በተናገርኸው መሠረት እስራኤላውያንን በእጄ የምታድናቸው ከሆነ፥ 37እነሆ፤ የበግ ጠጉር ባዘቶ በአውድማው ላይ አኖራለሁ። ምድሩ በሙሉ ደረቅ ሆኖ ባዝቶው ላይ ብቻ ጤዛ ቢኖር፥ እንዳልከው እስራኤላውያንን በእኔ እጅ እንደምታድናቸው አውቃለሁ።” 38እንደዚሁም ሆነ፤ ጌዴዎን በማግስቱ ጠዋት ማልዶ ተነሣ፤ ባዘቶውንም ሲጨምቅ የወጣው ውሃ አንድ ቆሬ ሞላ። 39ከዚያም ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “እባክህ አትቈጣኝ፤ አንዲት ጥያቄ እንደገና ልጠይቅ። በጠጉሩ ባዘቶ ላይ ሌላ ሙከራ እንዳደርግ ፍቀድልኝ፤ በዚህ ጊዜ ምድሩ ሁሉ በጤዛ ተሸፍኖ ባዘቶው ደረቅ ይሁን።” 40በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር እንደጠየቀው አደረገ፤ ባዘቶው ብቻ ደረቅ ሲሆን፥ ምድሩ በሙሉ በጤዛ ተሸፍኖ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ