መጽሐፈ መሳፍንት 5
5
የዲቦራና የባራቅ መዝሙር
1 #
ዘፀ. 15፥1። በዚያም ቀን ዲቦራና የአቢኒኤም ልጅ ባራቅ እንዲህ ብለው ተቀኙ፦
2በእስራኤል ውስጥ መሪዎች ስለ መሩ፥
ሕዝቡም ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ስለ ሰጡ፥
ጌታን አመስግኑ።
3ነገሥታት ሆይ፥ ስሙ፥
መኳንንት ሆይ፥ አድምጡ፥
እኔ ለጌታ እቀኛለሁ፥
ለእስራኤል አምላክ ለጌታ እዘምራለሁ።
4 #
ዘዳ. 33፥2፤ መዝ. 68፥8-9፤ ዕን. 3፥3-15። አቤቱ፥ ከሴይር በወጣህ ጊዜ፥
ከኤዶምያስም ሜዳ በተራመድህ ጊዜ፥
ምድሪቱ ተናወጠች፥ ሰማያቱም አንጠበጠቡ፥
ደመናትም ደግሞ ውኃን አንጠበጠቡ።
5ከእስራኤል አምላክ ከጌታ ፊት፥
በሲናው ጌታ ፊት ተራሮች ቀለጡ።
6 #
መሳ. 3፥31። በዓናት ልጅ በሻምጋር ዘመን፥
በያዔል ዘመን መንገዶች ተቋረጡ፥
መንገደኞች በስርጥ መንገድ ይሄዱ ነበር።#ኢሳ. 33፥8።
7አንቺ፥ ዲቦራ፥ እስክትነሽ ድረስ፥
ለእስራኤልም እናት ሆነሽ እስክትነሽ ድረስ፥
ኃያላን በእስራኤል ዘንድ አነሱ፥ አለቁም።
8አዲሶች አማልክትን መረጡ፥
በዚያ ጊዜ ሰልፍ በበሮች ሆነ፥
በአርባ ሺህ በእስራኤል ዘንድ ጦርና ጋሻ አልታየም።
9ልቤ ወደ እስራኤል አለቆች ነው፥
በሕዝቡ መካከል ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ወደ ሰጡት፥
ጌታን አመስግኑ።
10በነጫጭ አህዮች ላይ የምትጫኑ፥
በወላንሳ ላይ የምትቀመጡ፥
በመንገድም የምትሄዱ፥ ተናገሩ።
11በማጠጫው መካከል ካሉት ከቀስተኞች ጩኸት ርቀው፥
በዚያ የጌታን ጽድቅ፥
በእስራኤል ላይ የግዛቱን ጽድቅ ይጫወታሉ፥
ከዚያም በኋላ የጌታ ሕዝብ ወደ በሮች ወረዱ።
12ንቂ፥ ንቂ፥ ዲቦራ ሆይ፥
ንቂ፥ ንቂ፥ ቅኔውን ተቀኚ፥
ባራቅ ሆይ፥ ተነሣ፥
የአቢኒኤም ልጅ ሆይ፥ ምርኮህን ማርክ።
13በዚያ ጊዜ የቀሩት ወደ ኃያላኑና ወደ ሕዝቡ ወረዱ፥
ጌታም ስለ እኔ በኃያላን ላይ ወረደ።
14በአማሌቅ ዘንድ ሥር የነበራቸው እነርሱ ከኤፍሬም፥
ብንያም ሆይ፥ በሕዝብህ መካከል ከአንተ በኋላ ወረዱ፥
አለቆች ከማኪር፥ የንጉሥንም ዘንግ የሚይዙ ከዛብሎን ወረዱ።
15የይሳኮርም አለቆች ከዲቦራ ጋር ነበሩ፥
ይሳኮርም እንደ ባራቅ ነበረ፥
ከእግሩ በኋላ ወደ ሸለቆው ቸኰሉ፥
በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ብዙ የልብ ማመንታት ነበረ።
16መንጎች ሲያፍዋጩ ለመስማት
በበጎች ጉረኖ መካከል ለምን ተቀመጥህ?
በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ታላቅ የልብ ምርምር ነበረ።
17ገለዓድ በዮርዳኖስ ማዶ ተቀመጠ፥
ዳንም ለምን በመርከብ ውስጥ ቀረ?
አሴርም በባሕሩ ዳር ተቀመጠ፥
በወንዞቹም ዳርቻ ዐረፈ።
18 #
መሳ. 4፥10። ዛብሎን ነፍሱን ወደ ሞት ያሳለፈ ሕዝብ ነው፥
ንፍታሌምም በአገሩ ኮረብታ ላይ ነው።
19ነገሥታት መጡ፥ ተዋጉም፥
በዚያ ጊዜ በመጊዶ ውኆች አጠገብ በታዕናክ
የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፥
የብር ዘረፋም አልወሰዱም።
20 #
መሳ. 4፥15። ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፥
በአካሄዳቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ።
21 #
መሳ. 4፥7፤ 13፤ መዝ. 83፥10። ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥
የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው።
ነፍሴ ሆይ፥ በኃይል እርገጪ።
22ከኃያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣ
የፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ።
23የጌታ መልአክ፦ ሜሮዝን እርገሙ፥
ጌታን በኃያላን መካከል ለመርዳት፥
ጌታን ለመርዳት አልመጡምና
የተቀመጡባትን ሰዎች ፈጽማችሁ እርገሙ አለ።
24 #
መሳ. 4፥17፤ ዮዲ. 13፥18፤ ሉቃ. 1፥42። የቄናዊው የሔቤር ሚስት ያዔል
ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፥
በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን።
25 #
መሳ. 4፥19። ውኃ ለመነ፥ ወተትም ሰጠችው፥
በተከበረ ጽዋ እርጎ አቀረበችለት።
26 #
መሳ. 4፥21። እጅዋን ወደ ካስማ፥
ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፥
በመዶሻውም ሲሣራን መታች፥ ራሱንም ቸነከረች፥
ጆሮግንዱንም በሳች፥ ጎዳችውም።
27በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ ተኛ፥
በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥
በተደፋበት ስፍራ በዚያ ወድቆ ሞተ።
28ከመስኮት ሆና ተመለከተች፥
የሲሣራ እናት በሰቅሰቅ ዘልቃ፦
“ስለምን ለመምጣት ሠረገላው ዘገየ?
ስለ ምንስ የሠረገላው መንኰራኵር ቈየ?” ብላ ጮኸች።
29ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፥
እርሷ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች፦
30“ምርኮ አግኝተው የለምን? ተካፍለውስ የለምን?
ለእያንዳንዱ ሰው ምርኮ አንዲት ወይም ሁለት ቈነጃጅት፥
ለሲሣራ ምርኮ ልዩ ልዩ ያለው ልብስ፥
በአንገትጌ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጉርጉር ልብስ።”
31 #
መዝ. 83። አቤቱ፥ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፥
ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፥ እንዲሁ ይሁኑ። ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች።#መሳ. 3፥11፤30፤ 8፥28።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 5: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ