መጽሐፈ መሳፍንት 3:1-27

መጽሐፈ መሳፍንት 3:1-27 መቅካእኤ

በዚህ ጊዜ በከነዓን ላይ በተደረጉት ጦርነቶች ተሳትፈው የማያውቁትን እስራኤላውያን ለመፈተን፥ ጌታ ባሉበት የተዋቸው ሕዝቦች እነዚህ ናቸው። ይህን ማድረጉ ቀደም ሲል በጦር ሜዳ ውለው የማያውቁትን የእስራኤል ልጆች የጦርነት ልምድ እንዲያገኙ ለማድረግ ብቻ ነው። እነዚህም አሕዛብ አምስቱ የፍልስጥኤም ገዦች፥ ከነዓናውያን በሙሉ፥ ሲዶናውያንና ከበኣል አርሞንዔም ተራራ እስከ ሐማትስ መግቢያ ባሉት የሊባኖስ ተራሮች የሚኖሩ ኤዊያውያን ነበሩ። እነርሱም ጌታ በሙሴ አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻቸው የሰጣቸውን ትእዛዞች እስራኤላውያን ያከብሩ ወይም አያከብሩ እንደሆነ ለማወቅ ለእስራኤል መፈተኛዎች ነበሩ። ስለዚህ እስራኤላውያን ከከነዓናውያን፥ ከኬጢያውያን፥ ከአሞራውያን፥ ከፌርዛውያን፥ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን ጋር አብረው ኖሩ። እስራኤላውያን የእነዚህን ሴቶች ልጆች አገቡ፤ የራሳቸውንም ሴቶች ልጆች ለእነርሱ ወንዶች ልጆች ዳሩ፤ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ። እስራኤላውያን በጌታ ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ አምላካቸውን ጌታንም ረሱ፤ በኣልንና አስታሮትን አመለኩ። ጌታ በእስራኤላውያን ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ስለዚህ ለመስጴጦምያ ንጉሥ ለኩሽን-ሪሽዓታይም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እስራኤላውያንም ለኩሽን-ሪሽዓታይም ስምንት ዓመት በባርነት ተገዙለት። እስራኤላውያን ወደ ጌታ በጮኹ ጊዜ ግን፥ ጌታ የካሌብን ታናሽ ወንድም የቄኔዝን ልጅ ዖትኒኤልን ታዳጊ አድርጎ አስነሣላቸው። የጌታም መንፈስ በእርሱ ላይ ዐደረ፤ በእስራኤልም ላይ መሪ ሆነ፤ ለጦርነት በወጣ ጊዜ ጌታ የመስጴጦምያውን ንጉሥ ኩሽን ሪሽዓታይምን አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም ኩሽን-ሪሽዓታይምን ድል አደረገው። የቄኔዝ ልጅ ዖትኒኤል እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ምድሪቱ ለአርባ ዓመት ሰላም አገኘች። እስራኤላውያን እንደገና በጌታ ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ ይህን ክፋት በጌታ ፊት በማድረጋቸው፥ ጌታ የሞዓብ ንጉሥ ዔግሎን በእስራኤል ላይ እንዲበረታባቸው አደረገ። እርሱም አሞናውያንንና አማሌቃውያንን ካስተባበረ በኋላ እስራኤልን ወግቶ የዘንባባ ዛፎችበ ከተማ የሆነችውን ኢያሪኮን ያዙ። እስራኤላውያንም ለሞዓብ ንጉሥ ለዔግሎን ዐሥራ ስምንት ዓመት ተገዘሉት። እስራኤላውያን እንደገና ወደ ጌታ ጮኹ፤ ጌታም ብንያማዊውን የጌራን ልጅ፥ ግራኙን፥ ኤሁድን ነጻ እንዲያወጣቸው አስነሣው። እስራኤላውያን ኤሁድን ግብር አስይዘው ወደ ሞዓብ ንጉሥ ወደ ዔግሎን ላኩት። እርሱም በሁለት በኩል ስለታም የሆነና አንድ ክንድ ተኩል ርዝመትተ ያለው ሰይፍ አዘጋጅቶ በልብሱ ውስጥ በቀኝ ጭኑ ላይ አሰረው። ግብሩንም ወፍራም ለነበረው ለሞዓብ ንጉሥ ለዔግሎን አቀረበ። ኤሁድ ግብሩን ካቀረበ በኋላ፥ ግብር ተሸክመው የመጡትን ሰዎች ተመልሰው እንዲሄዱ አደረገ። እርሱ ራሱ ግን ጌልጌላ አጠገብ ድንጋዮች ተጠርበው ከሚወጡበት አካባቢ ሲደርስ ወደ ኋላ በመመለስ ወደ ንጉሡ ሄዶ፥ “ንጉሥ ሆይ፤ በምስጢር የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው። ንጉሡም፥ “ጸጥታ” ሲል፤ አጠገቡ የነበሩትአገልጋዮች በሙሉ ትተውት ወጡ። ንጉሡ ሰገነት ላይ ባለው ነፋሻ ዕልፍኝ ውስጥ ብቻውን ተቀምጦ ሳለ ኤሁድ ቀረብ ብሎ፥ “ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአንተ ያመጣሁት መልእክት አለኝ” አለው፤ ንጉሡም ከዙፋኑ ተነሣ። ኤሁድ ግራ እጁን ሰደድ በማድረግ ሰይፉን ከደበቀበት ከቀኝ ጭኑ መዝዞ በንጉሡ ሆድ ሻጠው። እጀታው ሳይቀር ሰይፉ እንዳለ ሆዱ ውስጥ ገባ፤ ሞራውም ስለቱን ሸፈነው፤ ስለቱም በጀርባው ወጣ፤ ኤሁድ ሰይፉን ስላልነቀለው አንጀቱ ተዘረገፈ። ከዚያም በኋላ ኤሁድ በዕልፍኙ መግቢያ ወጣ፤ የዕልፍኙንም በር በንጉሡ ላይ ዘግቶ ቈለፈው። ኤሁድ ከሄደ በኋላ፥ የንጉሡ አገልጋዮች ሲመጡ፥ የዕልፍኙ በር ተቈልፎ አገኙት፤ እነርሱም፥ “በውስጠኛው ክፍል እየተጸዳዳ ይሆናል” አሉ፤ እስኪደክማቸውም ድረስ ጠበቁ፤ ነገር ግን ንጉሡ የእልፍኙን በሮች ባለመክፈቱ ቊልፍ ወስደው ከፈቱ፤ በዚያም ጌታቸው ሞቶ፥ በወለሉም ላይ ተዘርግቶ አገኙት። የንጉሡ አገልጋዮች በዕልፍኙ በር ላይ ቆመው ሲጠባበቁ ኤሁድ ርቆ ሄደ፤ ድንጋዮች ተጠርበው በሚወጡበት በኩል ወደ ሴርታ ይም አመለጠ። እዚያም እንደ ደረሰ፥ በኰረብታማው በኤፍሬም ምድር ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ እስራኤላውያንም በእርሱ መሪነት ከኰረብታው ላይ አብረውት ወረዱ።