ትንቢተ ኢሳይያስ 58
58
1በኃይልህ ጩኽ፥ አትቈጥብ፥ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፥ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር። 2ነገር ግን ዕለት ዕለት ይሹኛል፤ መንገዴንም ለማወቅ ይወድዳሉ፤ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውንም ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝቦች እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፤ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወዳሉ። 3“ስለምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም?” ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። 4እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ፤ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ለማሰማት ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። 5እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነው? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነው? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ እንዲያደርግ፥ ማቅንና አመድንም በበታቹ እንዲያነጥፍ ነው? በውኑ ይህን ጾም፥ በጌታ ዘንድ የተወደደ ቀን ብለህ ትጠራዋለህ? 6እኔስ የመረጥሁት ጾም፥ የበደልን እስራት እንድትፈቱ፥ የቀንበርንስ ጠፍር እንድትለቁ፥ የተገፉትን አርነት እንድታወጡ፥ ቀንበሩን ሁሉ እንድትሰብሩ አይደለምን? 7#ማቴ. 25፥34።እንጀራህንስ ለተራበ እንድትቈርስ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ እንድታስገባ፥ የተራቈተውን ብታይ እንድታለብሰው፥ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? 8የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የጌታም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል። 9የዚያን ጊዜ ትጠራለህ ጌታም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ እርሱም፦ እነሆኝ ይላል። ከመካከልህ ቀንበርን ብታርቅ፥ በጣትህም መጠቆም ብትተው፥ ባታንጐራጉርም፥ 10ነፍስህንም ለተራበ ብታፈስስ፥ የተጨነቀውንም ነፍስ ብታጠግብ፥ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል። 11ጌታም ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ነፍስህንም በመልካም ነገር ያጠግባል አጥንትህንም ያጠናል፤ አንተም እንደሚጠጣ ገነት፥ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ። 12ከዱሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎች ይሠራሉ፥ የብዙ ትውልድም መሠረት ይታነጻል፤ አንተም፦ ሰባራውን ጠጋኝ፥ የአውራ መንገድ አዳሽ ትባላለህ። 13ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ፥ እግርህን ወደ ሰንበት፥ ሰንበትንም ደስታ፥ ጌታንም የቀደሰውን ክቡር ብትለው፥ በራስህ መንገድህን ከመጓዝ፥ ፈቅድህንም ከመፈጸም፥ ከንቱ ነገርንም ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው፥ 14በዚያን ጊዜ በጌታ ደስ ይልሃል፥ በምድርም ከፍታዎች ላይ አወጣሃለሁ፥ የአባትህንም የያዕቆብን ርስት አበላሃለሁ፤ ይህን የጌታ አፍ ተናግሮአልና።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 58: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ