የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 44

44
1አሁንም አገልጋዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማ። 2የፈጠረህ ከማኅፀንም የሠራህ የሚረዳህም ጌታ እንዲህ ያልል፦ አገልጋዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም ይሹሩን ሆይ፥ አትፍራ። 3በተጠማ ላይ ውኃን በደረቅም መሬት ላይ ፈሳሾችን አፈሳለሁና፤ መንፈሴን በዘርህ ላይ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አፈሳለሁ፥ 4በፈሳሾችም አጠገብ እንደሚበቅሉ እንደ አኻያ ዛፎች በሣር መካከል ይበቅላሉ። 5ይህ፦ እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ይላል፥ ያም በያዕቆብ ስም ይጠራል፤ ይህም፦ እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ብሎ በእጁ ይጽፋል፤ በእስራኤልም የቁልምጫ ስም ይጠራል። 6#ኢሳ. 48፥12፤ ራእ. 1፥17፤ 2፥8፤ 22፥13።የእስራኤል ንጉሥ ጌታ፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔ ፊተኛ ነኝ፥ እኔ ፍጻሜም ነኝ፤ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም። 7እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ይነሣና ይጥራ ይናገርም፤ ከጥንት የፈጠርሁትን ሕዝብ ያዘጋጅልኝ፥ የሚመጣውም ነገር ሳይደርስ ይንገረኝ። 8አትፍሩ አትደንግጡም፤ ከጥንቱም ጀምሬ አልነገርኋችሁም? ወይስ አላሳየኋችሁም? እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ ሌላ አምላክ አለን? ሌላ ዐለት የለም፤ አንድም አላውቅም።
የጣዖት አምላኪዎች ከንቱነት
9የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩ ከንቱዎች ናቸው፤ የወደዱትም ነገር አይጠቅማቸውም፤ ምስክሮቻቸውም አያስተውሉም ደግሞ አያውቁም፥ ስለዚህ ያፍራሉ። 10ጣዖትን የሠራ ወይስ ለምንም የማይረባን ምስልን የቀረጸ ማን ነው? 11እነሆ፥ ባልንጀሮቹ ሁሉ ያፍራሉ፥ ባለሙያዎቹም ከሰው ወገን ናቸው፤ ሁሉም ተሰብስበው ይቁሙ፤ ይፈራሉ በአንድነትም ያፍራሉ። 12ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይሠራል፥ በፍምም ውስጥ ያደርገዋል፥ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሠጠዋል፤ በክንዱም ኃይል ይሠራዋል፥ እርሱም ይርበዋል ይደክማልም፤ ውኃም ለመጠጣት ይታክታል። 13ጠራቢው ገመድ ይዘረጋል፥ በጠመኔም ምልክት ያኖራል፥ በመሮም ይቀርጸዋል፥ በመለኪያም ይለከዋል፤ በቤትም ውስጥ እንዲቀመጥ በሰው አምሳልና በሰው ውበት ይቀርጸዋል። 14የዝግባን ዛፎች ይቈርጣል፤ የዞጲንና የኮምቦልን ዛፍ ይመርጣል፥ ከዱር ዛፎችም መካከል እንዲጠነክር ይተወዋል፤ የጥድንም ዛፍ ይተክላል፥ ዝናብም ያበቅለዋል። 15#ጥበ. 13፥11-19።ለሰውም ማገዶ ይሆናል፤ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፥ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፤ ከእርሱም አምላክ አበጅቶ ይሰግድለታል፤ የተቀረጸውንም ምስል ሠርቶ በእርሱ ፊት ይንበረከካል። 16ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፥ በዚያ በግማሹ ሥጋ ይበላል፤ ሥጋም ይጠብስበትና ይጠግባል፤ ይሞቃልና፦ “እሰይ ሞቅሁ፥ ሙቀት ተሰማኝ” ይላል። 17የቀረውንም እንጨት አምላክ አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፤ በፊቱም ተጐንብሶ ይሰግድበታል፤ ወደ እርሱም እየጸለየ፦ አምላኬ ነህና አድነኝ ይላል። 18አያውቁም፥ አያስቡም፤ እንዳያዩ ዐይኖቻቸውን፥ እንዳያስተውሉም ልቦቻቸውን ጨፍነዋል። 19በልቡም ማንም አያስብም፦ “ግማሽዋን በእሳት አቃጥያለሁ፥ በፍምዋም ላይ እንጀራን ጋግሬአለሁ፥ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ፤ የቀረውንም አስጸያፊ ነገር አደርጋለሁን? ለዛፍስ ግንድ እሰግዳለሁን?” ለማለት እንኳን እውቀትና ማስተዋል የለውም። 20አመድ ይበላል፥ የተታለለ ልብ አስቶታል፥ ነፍሱን ለማዳን አይችልም፥ ወይም፦ “በቀኝ እጄ ሐሰት አለ?” ብሎም አይጠይቅም። 21ያዕቆብ ሆይ፥ አንተም እስራኤል፥ አገልጋዬ ነህና ይህን አስብ፤ እኔ ሠርቼሃለሁ አንተም አገልጋዬ ነህ፤ እስራኤል ሆይ፥ በእኔ ዘንድ ያልተረሳህ ትሆናለህ። 22መተላለፍህን እንደ ደመና፥ ኃጢአትህንም እንደ ጭጋግ ደምስሼአለሁ፤ ተቤዥቼሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ። 23ሰማያት ሆይ፥ ጌታ አድርጎታልና ዘምሩ፤ ጌታ ያዕቆብን ተቤዥቶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና አንተ የምድር ጥልቅ ሆይ፥ ጩኽ፤ እናንተም ተራሮች አንተም ዱር በአንተም ያለ ዛፍ ሁሉ፥ እልል በሉ። 24ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ ጌታ እኔ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ማን ነበረ? 25#1ቆሮ. 1፥20።የሐሰተኞችን ምልክት ከንቱ አደርጋለሁ፥ ምዋርተኞችንም አሳብዳለሁ፥ ጥበበኞቹንም ወደ ኋላ እመልሳለሁ፥ እውቀታቸውንም ስንፍና አደርጋለሁ፤ 26የባርያዬን ቃል አጸናለሁ፤ የመልእክተኞቼንም ምክር እፈጽማለሁ፤ ኢየሩሳሌምን፦ የሰው መኖሪያ ትሆኛለሽ፥ የይሁዳንም ከተሞች፦ ትታነጻላችሁ ፍራሾቻችሁንም አቆማለሁ እላለሁ። 27ቀላዩም፦ “ደረቅ ሁን፥ ፈሳሾችህንም አደርቃለሁ” እላለሁ፤ 28#2ዜ.መ. 36፥23፤ ዕዝ. 1፥2።ቂሮስንም፦ “እርሱ እረኛዬ ነው”፤ እርሱም ኢየሩሳሌምን፦ “ትታነጺያለሽ ቤተ መቅደስም ይመሠረታል” ይላል፤ እኔም “ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል” እላለሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ