ትንቢተ ኢሳይያስ 45
45
1ጌታ ለቀባው፥ አሕዛብንም በፊቱ እንዲገዙለት፥ የነገሥታትንም ወገብ እዲፈታ፥ በሮቹም እንዳይዘጉ መዝጊያዎቹ በፊቱ እንዲከፈቱለት፥ ቀኝ እጁን ለያዘው ለቂሮስ እንዲህ ይላል፦ 2በፊትህ እሄዳለሁ ተራሮችንም እደለድላለሁ፥ የናሱንም ደጆች እሰብራለሁ የብረቱንም መወርወሪያዎች እቈርጣለሁ፤ 3በስምህም የምጠራህ የእስራኤል አምላክ ጌታ እኔ እንደሆንሁ ታውቅ ዘንድ በጨለማ የነበረችውን መዝገብ በስውርም የተደበቀችውን ሀብት እሰጥሃለሁ። 4ስለ አገልጋዬ ስለ ያዕቆብ፥ ስለ መረጥሁትም ስለ እስራኤል ብዬ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ በቁልምጫ ስምህ ጠራሁህ፥ አንተ ግን አላወቅኸኝም። 5እኔ ጌታ ነኝ፥ ከእኔም ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔም በቀር አምላክ የለም፤ አንተ ባታውቀኝም እኔ አስታጠኩህ፤ 6በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ፥ ከእኔ በቀር ማንም ሌላ እንደሌለ ይወቁ እኔ ጌታ ነኝ፥ ከእኔም ሌላ ማንም የለም። 7ብርሃንን ሠራሁ፥ ጨለማውንም ፈጠርሁ፤ አበለጽጋለሁ፤ አደኸያለሁ፤ ይህን ሁሉ የማደርግ እኔ ጌታ ነኝ። 8እናንተ ሰማያት ከላይ አንጠባጥቡ ደመናትም ጽድቅን ያዝንቡ፤ ምድርም ትከፈት መድኃኒትንም ታብቅል፥ ጽድቅም በአንድነት ይብቀል፤ እኔ ጌታ ፈጥሬዋለሁ። 9#ኢሳ. 29፥16፤ ሮሜ 9፥20።ከሠሪው ጋር ለሚታገል ወዮለት! በምድር ሸክላዎች መካከል ያለ ሸክላ ነው። ጭቃ ሠሪውን፦ ምን ትሠራለህ? ወይስ ሥራህ እጅ የለውም ይላልን? 10አባትን፦ ምን ወልደሃል? ወይም ሴትን፦ ምን አማጥሽ? ለሚል ወዮ! 11የእስራኤል ቅዱስ ሠሪውም ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለሚመጣው ነገር ጠይቁኝ፥ ስለ ልጆቼና ስለ እጄ ሥራም እዘዙኝ። 12እኔ ምድርን ሠርቻለሁ ሰውንም በእርሷ ላይ ፈጥሬአለሁ፤ እኔ በእጄ ሰማያትን ዘርግቻለሁ፥ ሠራዊታቸውንም ሁሉ አዝዣለሁ። 13እኔ በጽድቅ አስነሥቼዋለሁ መንገዱንም ሁሉ አቀናለሁ፤ እርሱ ከተማዬን ይሠራል፥ በዋጋም ወይም በደመወዝ ሳይሆን ምርኮኞቼን ያወጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። 14ጌታ እንዲህ ይላል፦ የግብጽ ድካምና የኢትዮጵያ ንግድ ቁመተ ረጅሞችም የሳባ ሰዎች ወደ አንተ ያልፋሉ፤ ለአንተም ይሆናሉ እጆቻቸውም ታስረው ይከተሉሃል፤ በፊትህም ያልፋሉ፥ ለአንተም እየሰገዱ፦ በእውነት እግዚአብሔር በአንተ አለ፥ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም ብለው ይለምኑሃል። 15የእስራኤል አምላክ መድኃኒት ሆይ፥ በእውነት አንተ ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ። 16ሁሉም ያፍራሉ ይዋረዱማል፥ ጣዖታትንም የሚሠሩ በአንድነት ወደ ውርደት ይሄዳሉ። 17ጌታ ግን እስራኤልን በዘላለማዊ መድኃኒት ያድነዋል፥ እናንተም ለዘለዓለም አታፍሩምና አትዋረዱም። 18ሰማያትን የፈጠረ ጌታ፥ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፥ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፥ እንዲህ ይላል፦ እኔ ጌታ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም። 19በስውር ወይም በጨለማ ምድር አልተናገርሁም፤ ለያዕቆብ ዘር፦ በከንቱ ፈልጉኝ አላልሁም፤ እኔ ጌታ እውነትን እናገራለሁ ትክክለኛውንም አወራለሁ። 20እናንተ ከአሕዛብ ወገን ሆናችሁ ያመለጣችሁ፥ ተሰብስባችሁ ኑ በአንድነትም ቅረቡ፤ የተቀረጸውን የምስላቸውን እንጨት የሚሸከሙና ያድን ዘንድ ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ እውቀት የላቸውም። 21ይናገሩ ይቅረቡም በአንድነትም ይማከሩ፤ ከጥንቱ ይህን ያሳየ ከቀድሞስ የተናገረ ማን ነው? ያሳየሁም የተናገርሁም እኔ ጌታ አይደለሁምን? ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኃኒት ነኝ፥ ከእኔም በቀር ማንም የለም። 22እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ። 23#ሮሜ 14፥11፤ ፊልጵ. 2፥10-11።ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፥ አትመለስም፦ ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፥ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ። 24ስለ እኔም፦ በጌታ ዘንድ ብቻ ጽድቅና ኃይል አለ፥ ወደ እርሱም ሰዎች ይመጣሉ፥ በእርሱም ላይ የተቆጡ ሁሉ ያፍራሉ። 25የእስራኤልም ዘር ሁሉ በጌታ ይጸድቃሉ፥ ይመካሉም ይከብራሉም።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 45: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ